የፌዴራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን አገልግሎት ለመጀመር መዘጋጀቱን ገለጸ

147

አዲስ አበባ መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) የፌዴራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ለመንግስት አልሚ ድርጅቶች ተቋማዊ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ ይህን የገለጸው አጠቃላይ ዝግጅቱ ለመንግስት አልሚ ድርጅቶች ባዘጋጀው የትውውቅ መድረክ ነው።

በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ በገባበት ባለፈው አንድ ዓመት የሰው ሀብትና የተቋም ግንባታ ሥራዎችን ሲከውን መቆየቱን ለባለድርሻ አካላቱ ገልጿል። 

መረጃውን በተደራጀ የመሬት ይዞታ ቋት ለማደራጀት ከጂኦስፔሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በቅንጅት ሲሠራም ቆይቷል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን ለኢዜአ ሲናገሩ የትውውቅ መድረኩ የት እንዳለንና ምን እንደምንሠራ በማሳወቅ ሥራዎቻችን ላይ ትስስር ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ሰፋፊ የመሬት ይዞታዎችን ለማልማት ወስደው የሚያስተዳድሩ ድርጅቶች በሚፈለገው ልክ ለምቷል ወይ? የሚለውን በጋራ እንዲገመግሙ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍትም ጠቁመዋል።

ተቋማዊ የትብብር ማዕቀፉ ከግል ድርጅቶች ጋር ከሚኖረው የሁለትዮሸ የትብብር ማዕቀፍ ወደ "መንግስት-ለመንግስት"

የሚያሳድግና ውህደት ማስጀመሪያ መድረክ እንደሆነም አክለዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ መንግስት የመሬት ይዞታዎቹን ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች መጠቀም እንዲችል መሬት ያለበትን ደረጃ በማየት መልማት በሚችልበት ሁኔታ ዝግጅት ተደርጓል።

ኮርፖሬሽኑ አልሚዎች ትርፋማ መሆን እንዲችሉ የቢዝነስ ዕቅዳቸውን ከማማከር ጀምሮ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መስጠት በሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የአልሚ ድርጅቶቹ መሬት በምን ደረጃ እንደሚገኝ የማጥራት ሂደት በአዲስ አበባ መጀመሩንና ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚሰፋም አስታውቀዋል።

ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ባለፈው አንድ ዓመት እንቅስቃሴው የመሬት መረጃዎችን የማሰባሰብ ኦዲት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የፌዴራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በአዋጅ ቁጥር 1097/2010 የተቋቋመና በፌዴራል የመሬት ይዞታና አስተዳደር ሥርዓት ላይ የሚሰራ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም