ብሪታኒያ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ የክትባት ጥምረት 500 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ ልታደርግ ነው

106

አዲስ አበባ መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) የብሪታኒያ መንግስት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት ተደራሽ ማድረግን ዓላማ ላደረገው ጥምረት 500 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

ዓለም አቀፉን ወረርሽኝ ለመግታት ለሁሉም አገራት ፈጣን፣ ፍትሐዊና እኩል የኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽነትን ዓላማ ያደረገው ጥምረት /ኮቫክስ/ በሐምሌ 2012 ዓ.ም መመሥረቱ ይታወቃል።

የበለጸጉ አገራት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ካላቸው ጋር በመተባበር በቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን አማካኝነት በተቋቋመው በጋቪ የክትባት ጥምረት በተዘጋጀ ፕሮጀክት የክትባት ተደራሽነትን ለማስፋት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ።

የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ትናንት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 75ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር መንግስታቸው ለጥምረቱ 500 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ድጋፉ በግንቦት 2012 ዓ.ም በብሪታኒያ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የክትባት ጉባዔ መንግስታቸው ለጥምረቱ አደርገዋለሁ ካለው የ48 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ በተጨማሪ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ዝቅተኛና በዝቅተኛ መካከለኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ተብለው የተለዩ 92 አገራት በጥምረቱ አማካኝነት ክትባት የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻች መናገራቸውን በኢትዮጵያ የብሪታኒያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የገንዘብ ድጋፉ በማድረግ ላይ የሚገኙ አገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል ዓለም አቀፍ ስርጭቱን በመግታት ሁላችንም ደህና እንድንሆን ያግዛል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ብሪታኒያ በዝቅተኛ እንዲሁም በዝቅተኛ መካከለኛ ደረጃ ለሚገኙ አገራት ከምታደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በጥምረቱ አማካኝነት 71 ሚሊዮን ፓውንድ የመነሻ ገንዘብ አስተዋጽኦ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

የገንዘብ ድጋፉ ለ27 ሚሊዮን ዜጎቿ ክትባት ተደራሽ ማድረግን ግብ ያደረገ መሆኑንም ነው ቦሪስ ጆንሰን የገለጹት።

በሌላ በኩል ብሪታኒያ ለዓለም ጤና ድርጅት እ.አ.አ 2021 ጨምሮ ለአራት ዓመታት 340 ሚሊዮን ፓውንድ የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቁመዋል።

ይህም ብሪታንያ ባለፉት አራት ዓመታት ለድርጅቱ ካደረገችው ድጋፍ የ30 በመቶ ብልጫ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ብሪታኒያ እ.አ.አ 2021 በቡድን ሰባት አባል አገራት የሚኖራትን የፕሬዚዳትነት ሚና ተጠቅማ በዓለም አቀፍ የጤና ቀውስን አዲስ ፈጠራ በታከለበት መልኩ መከላከል የሚያስችል የአምስት ነጥብ እቅድ ተግባራዊ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰትን ወረርሽኝ ቀድሞ ማወቅ የሚያስችል ዓለም አቀፍ የእንስሳት ጥናትና ምርምር ማዕከላት ጥምረት ማቋቋም የመጀመሪያው ዕቅድ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ክትባቶችና መድሐኒቶች የማምረት አቅምን ማሳደግ፣ የሚከሰቱ የጤና ቀውሶችን ለማወቅ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት መዘርጋት፣ ለዓለም አቀፍ የጤና አደጋዎች በጋራ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የአሰራር ስርዓትና መመሪያ ላይ ስምምነት መድረስና በሽታን ለመከላከል በሚገዙ የጤና ቁሳቁስ ላይ ያሉ የንግድ ገደቦችና ክልከላዎችን መቀነስ በዕቅዱ የሚካተቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ የፈጠረውን መከፋፈል ማሸነፍ ይገባዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ዓለም ቫይረሱን ማሸነፍ ከፈለገ በአንድነት መቆም አለበት ብለዋል።

በጋራ ጠላታችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ ካልተባበርን ተሸናፊ እንሆናለን ነው ያሉት።

ከዘጠኝ ወራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመዋጋት ሂደት በኋላ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የመሰላቸት ሁኔታ እየታየበት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በበይነ መረብ እየተካሄደ በሚገኘው የመንግስታቱ ድርጅት 75ኛ ጠቅላላ ጉባዔ የአገራት መሪዎች መልዕክቶቻቸውን እያስተላለፉ ይገኛሉ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባትን ተደራሽ ማድረግን ዓላማ ባደረገው ጥምረት አማካኝነት በሁለት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሁለት ቢሊዮን የክትባት መጠኖች በማምረት እ.አ.አ በ2021 ለአንድ ቢሊዮን ሰዎች ክትባት ተደራሽ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል።

እስካሁን ድረስ በዓለም ዙሪያ ጥቅም ላይ እንዲውል የተፈቀደ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የለም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም