በድሬዳዋ የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲከበር ፖሊስ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ

152

ድሬዳዋመስከረም 15/2013(ኢዜአ) የመስቀል ደመራ በዓል ያለምን የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ 

በኮሚሽኑ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር  ጉሌት ድሪዬ ነገ በድሬዳዋ ለገሀር አደባባይ የሚከበረው በዓል በሰላም እንዲከበር ፖሊስ ከከተማው ወጣቶች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ አደረጃጀት በመፍጠር ተሰናድቷል።

ይህም አንዳንድ ድብቅ ዓላማ ያነገቡ አካላት በዓሉን ለማወክ የሚደረግ እንቅስቃሴ ድንገት ከተፈጠረ  በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

ታዳሚዎች የተሰጣቸውን  የመግቢያ  ካርድ ለፀጥታ አካላት በማሳየት ለሰላሙ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፤ በዓሉን ሲያከብሩም ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከኮሮና በመከላከል ሊሆን እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ፖለቲካዊና ይዘት ያላቸው ፣ኃይማኖትን ከኃይማኖት የሚያጋጩ መልዕክቶችንና ዓርማዎችን ይዘው መግባት የተከለከለ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ይህ በአንዲህ እንዳለ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ-ትጉሃን ማትያስ በቀለ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የፍቅር የሰላምና የአንድት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን  የተቸገሩትን በመርዳት ፣ የታመሙትን በመጠየቅ እንዲያከብርም መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል፡፡

ዘንድሮ በሀገርም ሆነ በድሬዳዋ የኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ የጤናና ማህበራዊ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ ምዕመናኑን በዓሉን ሳያስከብሩ የአፍና የአፍንጫ ጭንብል በመልበስ ሊሆን እንደሚገባም መክረዋል።

ህዝበ ክርስቲያኑ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተባብሮ  ለሰላሙ ዘብ በመቆም እንዲንቀሳቀስም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም