ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የኢኮኖሚ ወንጀሎች የመከላከል ሥራውን ለማጠናከር ከፋይናስ ደሕንነት ማዕከል ጋር እየሰራ ነው

77

 አዲስ አበባ  መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የኢኮኖሚ ወንጀሎች የመከላከል ሥራውን ይበልጥ ለማሳደግ ከፋይናንስ ደህሕንነት ተቋም ጋር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ::

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከፋይናስ ደሕንነት ማዕከል ጋር እስካሁን በትብብር ሲሰራ የነበረውን ተግባር ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኩል ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ ፀጋዬ፤ በፋይናስ ደሕንነት ማዕከል በኩል ደግሞ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ቴዎድሮስ በቀለ ፈርመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ፍቃዱ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የኢኮኖሚ ወንጀሎችን በቅንጅት ለመከላከልና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ከአጋር አካላት ጋር እየተሰራ ነው።

ከዚህ ውስጥ ከፋይናንስ ደሕንነት ማዕከል ጋር እየተሰራ ያለው ሥራ አንዱ መሆኑንና አሁን የተደረገው ስምምነት የትብብር ሥራዎችን በተሻለ መልኩ ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።   

አቶ ፍቃዱ እንዳሉት ወንጀሉን ከመከላከል ባለፈ ፈጻሚዎች ያገኙትን ሃብት በማሳጣትና በማስተማር ረገድ ከተቋሙ ጋር የሚከናወኑ ተግባራትን የተሻለ ለማድረግም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

"በአሁኑ ወቅት በርካታ ወንጀሎች እየተፈጸሙ ያሉት ከገንዘብ ጋር በተገናኝ ነው" ያሉት አቶ ፈቃዱ፣ ከእነዚህ ውስጥ የሽብርተኝነት፣ ሕገወጥ የሰዎችና የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውሮች እንደሚጠቀሱ አመልክተዋል።

የፋይናንስ ደሕንነት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት እንዳሉት ተቋሙ ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

በእዚህም በፋይናንስ በኩል ሙያዊ ትንተናዎችን በመስጠትና ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀርቡ በማድረግ በኩል በጋራ እንደሚሰሩ ነው ያመለከቱት።

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የኢኮኖሚ ወንጀሎች ዳይሬክተር አቶ አንተነህ አያሌው የተቋሙን እስትራቴጂክ ዕቅድ በመድረኩ ሲያቀርቡ እንዳሉት፣ በ2012 በጀት ዓመት በርካታ የኢኮኖሚ ወንጀሎች ተፈጽመዋል።

በተለይም በግብር ስወራ፣ ያለደረሰኝ በሚካሔድ ግብይትና ከሸማቾች መብት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዋነኞቹ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

እንደ አቶ አንተነህ ገለጻ ወንጀል ፈጻሚዎችን ለሕግ ከማቅረብ አኳያ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።

በእዚሁ በጀት ዓመት የተገኙት ውጤቶች በተናጠል በተሰራ ስራ የተገኙ መሆናቸውን ጠቁመው ከሌሎች የፍትሕ አካላት ጋር በትብብር ከመስራት አኳያ በርካታ ተግዳሮቶች እንደነበሩም ተናግረዋል።

በቀጣይ የኢኮኖሚ ወንጀል ፈጻሚዎችን ተከታትሎ ለሕግ ለማቅረብ በየደረጃው ከሚገኙ የፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዕቅድ መያዙንም ዳይሬክተር አቶ አንተነህ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም