በሀዋሳ የደመራ በዓል ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ለማክበር ዝግጅት ተደረገ

78

ሀዋሳ፣ጅማ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ የደመራ ክብረ በዓል ኮሮናን ለመከላከል ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲከበር በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ቤተክርሲቲያኗ አስታወቀች፡፡

በተመሳሳይ በጅማ ከተማ  የመስቀል ደመራ በዓል እንደሚከበር ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀዋሳ ከተማና ዙሪያ ወረዳዎች ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ላዕከ ወንጌል ቀሲስ ደግፌ ባንቡራ እንደገለፁት ቤተክርስቲያኗ ከጥንትም ጀምሮ በሀገር ላይ ወረርሽኝ ሲከሰት ህዝቦቿን የመጠበቅና በፀሎት የማገዝ ኃላፊነቷን ስትወጣ ቆይታለች ፡፡

የአለም ፈተና የሆነው ኮሮና ከተከሰተ በኋላም ይህን ተግባሯን እያከናወነች እንደምትገኝ ገልጸው  ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት ስትተገብረው እንደቆየች፣ ከአዋጁ መነሳት በኋላም አጠናክራ መቀጠሏን ተናግረዋል፡፡

የደመራ ክብረ በዓል ኮሮናን ለመከላከል የሚደረግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲከናወንም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን  አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በከተማዋ በአንድ ቦታ ይከናወን የነበረው ክብረ በዓል የህዝብ መሰባሰብን ለመቀነስ ሁለት ስፍራዎች ላይ እንዲከናወን መደረጉን አመልከተው ምእመናንም አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ርቀታቸውን ጠብቀው በበዓሉ እንደሚታደሙ መክረዋል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ ሊደረጉ የሚገቡ የጥንቃቄዎች  በተመለከተ ይህንን ከሚያስተባብሩ የቤተክርስቲያኒቱ ወጣቶች ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩም አስረድተዋል።

የቤተክርስቲያኒቱን ወጣቶች አስተባባሪ ዲያቆን አንተነህ ጌትነት በበኩላቸው ለክብረ በዓሉ የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውኑ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ ከዚህ በፊትም በየአጥቢቸው የኮሮና ወረርሽኝን የመከላከልያ መንገዶች እንዲተገበሩ ሲሰሩ መቆየታቸውን አውስተው የደመራ በዓልም ይህንን መንገድ በተከተለ መልኩ እንዲከበር ኃላፊነት ወስደው እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ኤፍሬም ሲማኖ በዓሉ በከተማዋ በድምቀት እና ከፍተኛ ህዝብ በተሰበሰበበት ይከበር እንደነበር አስተውሰው በኮሮና ምክንያት ዘንድሮ እንደወትሮው ለማክበር አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ ከቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር በመናበብ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው በፀጥታው በኩልም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ ወደ ክብረ በዓሉ ስፍራ ሲመጣ ኮሮናን ለመከላከል መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች በአግባቡ እንዲተገብር ከሚያስተባብሩ ወጣቶች ጋር እየሰራን ነው ብለዋል ፡፡

በተመሳሳይ በጅማ ከተማ  የመስቀል ደመራ በዓል ላይ የተወሰኑ ሰዎች በሚሳተፉበት ስነ-ስርዓት እንደሚከበር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የየም፣ ጅማና ኮንታ ሀገረ ስብከት ኃላፊ መላከሰላም ተስፋሚካኤል አሰፋ  ገለጹ።

የተሳታፊዎች  ቁጥር መወሰን ያስገደደው  የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል መሆኑ ተናግረዋል።፡

ነገ በሚከበራው የመስቀል ዳመራ በዓል ላይ መሳተፍ የሚችሉትም ባጅ የተሰጣቸው ምዕምናን፣ የከተማና ዞን አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፣ ዲያቆናት፣መዘምራን መሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡

ተሳታፊዎች በዓሉ ወደ ሚከበርበት አዌቱ ማዘውተሪያ ሲገኙ የተሰጣቸውን ባጅ ፣የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግና ሳንታይዘር በመያዝ መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም