በዞኑ 1 ሺህ 700 ሄክታር የተፈጥሮ ደን ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገለት ነው

769

ሁመራ፣ መስከረም 15 /2013 (ኢዜአ ) በትግራይ ምዕራባዊ ዞን 1 ሺህ 700 ሄክታር የተፈጥሮ ደን በህብረተሰብ ተሳትፎ ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተስፋይ ጸሃየ ለኢዜአ እንደገለጹት  የተፈጥሮ ደን ጥበቃና እንክብካቤ እየተካሄደ ያለው በጸገዴ፣ቃፍታ ሁመራና ወልቃይት ወረዳዎች ነው።

በዞኑ የእርሻ ኢንቨስትመንት መስፋፋት፣ የግንባታና ማገዶ ፍላጎት መጨመርን  ተከትሎ በደን ይዞታዎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ውድመት ለመከላከል ተከልሎ እንዲጠበቅ መደረጉን ተናግረዋል ።

ባለፈው ዓመት በደን ይዞታው ውስጥ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞች ተተክለው 71 በመቶው መጽደቃቸውን ጠቅሰዋል ።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ ማህበረሰብ አቀፍ የደን ጥበቃና እንክብካቤ ስራው እየተካሄደ ያለው ሬድ ፕላስና ኤስ. ኤል. ኤስ  በተባሉ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ትብብር ነው።

በቃፍታ ሁመራ ወረዳ ባዕከር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በርሀ ገብረገርግስ  በደን ጥበቃና እንክብካቤው ስራ እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በአካባቢው ለሚገኘው የተፈጥሮ ደን ጥበቃ ከማድረግ ባለፈ በደን ይዞታው ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

“ህብረተሰቡ ለተፈጥሮ ደን ጥበቃ ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ መጥቷል” ያሉት ደግሞ በወረዳው ሕለት ኮካ ቀበሌ ነዋሪና የደን ጥበቃ ሰራተኛ አቶ ዑቁባይ ጎማ ናቸው ።

ከዚህ ቀደም በደን ላይ ይደርስ የነበረው ጭፍጨፋ እየተቀየረ መምጣቱን ተናግረዋል ።