ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ለኮሮናቫይረስ ስርጭት መስፋፋት ምክንያት እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ለኮሮናቫይረስ ስርጭት መስፋፋት ምክንያት እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል

አዲስ አበባ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) በሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ሳቢያ የሚደረጉ መሰባሰቦች ለኮሮናቫይረስ ስርጭት መስፋፋት ምክንያት እንዳይሆኑ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሐረላ አብዱላሂ በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ማህበራዊ መሰባሰቦች ለኮሮናቫይረስ ስርጭት መስፋፋት ምክንያት የሆኑበት አጋጣሚዎች ነበሩ።
በመሆኑም "በቅርቡ የሚከበሩት የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በአደባባይ በሰዎች መሰባሰብ የሚከበሩ በመሆናቸው ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሁኔታን እንዳይፈጠር ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።
አስገዳጅ ሆኖ በዓል ለማክበር ወደ አደባባይ የሚወጡ የእምነቱ ተከታዮችም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ህብረተሰቡም ከሃይማኖት አባቶች፣ ከጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ከአባ ገዳዎች የሚሰጡትን ምክረ ሃሳቦች በአግባቡ መተግበር እንዳለበት ነው ወይዘሮ ሰሐረላ ያስታወቁት።
"ከጊዜ ወደጊዜ በአገሪቱ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ የቫይረሱ ስርጭት እስከሚቆም ድረስ ህብረተሰቡ በዓላትን በቤት ውስጥ ማክበር እንዳለበት ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የቫይረሱ ስርጭት ቀድሞ ከነበረበት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም ከአንድ ወር በፊት 6 ሺህ ሰው ተመርምሮ በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ቁጥር ከ400 እንደማይበልጥና በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ሰው ተመርምሮ የሚያዙት ከ600 መብለጣቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
"ይህም የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መሆኑን ስለሚያሳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ ኮሮናቫይረስ በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በቅርቡ አንዳንድ ክልከላዎች በመንግስት እንዲነሱ ተደርጓል።
"ይህንን ተከትሎም በርካቶች ኮሮናቫይረስ ጠፍቷል በሚል መዘናጋት አሳይተዋል" ብለዋል።
"ይሁንና ክልከላዎቹ የተነሱት ቫይረሱ የሚያሳድረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት እንጂ የቫይረሱ ስርጭት ቆሞ እንዳልሆነ ህብረተሰቡ ልብ ሊል ይገባል" ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታዋ አመልክተዋል።
በቅርቡ የትምህርት ተቋማት ሲከፈቱ ተገቢውን ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተለይ ወላጆች ለልጆቻቸው ስለኮሮናቫይረስ ተገቢ ግንዛቤ እንዲጨብጡና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከወዲሁ ማስተማር እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።
በመጨረሻም ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሰሐረላ ለእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።