የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው ጥፋት ፈጽመዋል የተባሉ 73 ግለሰቦች የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው

502

ነገሌ፣መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ጉጂ ዞን የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በሰው አካልና ንብረት ላይ ጉዳት ፈጽመዋል ተብለው የተከሰሱ 73 ግለሰቦች እስከ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የዞኑ አስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደስታ ኤተና ግለሰቦቹ በፈጠሩት ሁከትና ግርግር  በ82 ሰዎች  ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል ብለዋል።

71 የመኖሪያ ቤቶችን በእሳት ማቃጠላቸውን፣ 89 ግልሰቦችን መዘረፋቸውንና በርካታ ተሽከርካሪዎችን ማውደማቸውንም ጭምር በሰነድና የሰው ማስረጃ  እንደተረጋገጠባቸው አስረድተዋል።

የንብረት ጥፋቱ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ጠቅሰው ድርጊቱ የተፈጸመው ከ2010 ዓ.ም እስከ 2011/2012 በጀት ዓመት ውስጥ እንደሆነ  አመልክተዋል፡፡

የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተደረገ ክትትል የጥፋቱ ተሳታፊ ናቸው ተብለው በህግ ቁጥጥር ስር ከዋሉት 152 ግለሰቦች መካከል 73ቱ  ጉዳያቸውን በማጣራት አቃቢ ህግ ክስ መስርቶባቸው ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው አስረድተዋል።

የምዕራብ ጉጂ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግለሰቦቹን ጉዳይ ሲመለከት ቆይቶ በተለያዩ ጊዜያት በዋለው ችሎት የጥፋቱ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች  በእድሜ ልክ፣ በተባባሪነት የተሳተፉ ደግሞ ከ6 ወር እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል ብለዋል፡፡

የተዘረፈውን ንብረት ከማስመለስ ጎን ለጎን በመንግስትና በህዝብ ትብብር ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ ሲከናወን መቆየቱን አብራርተዋል፡፡

የዞኑ ህዝብ የጥፋት ኃይሎችን በማጋለጥ ለህግ አሳልፎ መስጠት በመጀመሩ በአንዳንድ አካባቢዎች የነበረው አለመረጋጋት አሁን ሙሉ በሙሉ  ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሱን  አቶ ደስታ አብራርተዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈሪ ወንዳፈረው በበኩላቸው ለሰላማዊ ትግል የተመቻቸውን የፖለቲካ ምህዳር ለጥፋት ተግባር ማዋል አሳዛኝ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ ከአሁን  በኋላ የሰው ህይወትና መሰረተ ልማት እያጠፉ  እንዲሁም ንብረት እየዘረፉና እያቃጠሉ በኦሮሞ ህዝብ ስም የመነገድ አጀንዳ የተዘጋ መሆኑን አስታወቀዋል፡፡

የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ብሄር ብሄረሰቦችን እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚቀሰቅሱ የጥፋት ኃይሎች የዞኑ ህዝብ በቃ ሊላቸው እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የዞኑ ህዝብና የፍትህ አካላት በጥፋት ኃይሎች ላይ ለሚወስዱ ህጋዊ እርምጃዎች መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል፡፡

አሁን የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ህዝቡ የጀመረውን የጥፋት ኃይሎችን የማጋለጥ ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡