በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የተከናወኑ የለውጥ እና የህግ ማስከበር ሥራዎች የተሳኩ ነበሩ

77

አዲስ አበባ ፣መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የተከናወኑ የለውጥ ተግባራትና የህግ ማስከበር ሥራዎች የተሳኩ እንደነበር ተገለጸ።

አገሪቱ በ2012 ዓ.ም ያከናወነቻቸውን የለውጥ ተግባራት፣ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተሰሩ ሥራዎችንና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም እና በጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ አማካኝነት መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

በመግለጫው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያገኙት የኖቤል ሸልማት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ሥራዎች፣ የሕዳሴው ግደብ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ሥራ፣ የሸገር እና የአንድነት ፓርክ ግንባታ እንዲሁም በብዝሃ ፖለቲካ ስርዓት ግንባታ ላይ የተከናወኑ ተግባራት ጎልተው መውጣታቸው ተገልጿል፡፡

በአገሪቱ የሚታየውን ህገወጥ የሰዎች፣ የገንዘብ አና የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመቆጣጠር የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩም ኃላፊዋ ቢልለኔ ስዩም ተናግረዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ የግብርና ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የተሄደበት ርቀትም አመርቂ ነበር፡፡

የንግድ ስርዓቱንና የገቢ አሰባሰቡን ቀልጣፋ ለማድረግ የተጀመረው የኦንላይን ምዝገባ ውጤታማ እንደነበረም በመግለጫው ተመልክቷል።

"በአገሪቱ የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የተከናወነው አገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻም የታሰበለትን ግብ መቷል" ብለዋል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ ፡፡

መንግስት በመላ አገሪቱ 54 የምርመራ ማዕከላት በመገንባት የተሳካ ምርመራ ማድረግ የተቻለ ሲሆን የመመርመሪያ ኪት ማምረቻ በአገሪቱ በመገንባት ሂደቱን ለማቀላጠፍም ጥረት መደረጉ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኮቪድ -19 የምርመራ ውጤት በ24 ሰዓታት ውስጥ መግለጽ የተቻለ ሲሆን የለይቶ ማቆያ ሥፍራዎችም በበቂ ሁኔታ መዘጋጀታቸው በመልካም ተግባር እንደሚጠቀሱም ጠቁመዋል፡፡

በዲፕሎማሲው መስክ በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑና በውጭ አገር በችግር ላይ የነበሩ በርካታ ዜጎችን ወደ አገራቸው መመለስ መቻሉም እንዲሁ በመግለጫው ተነስቷል፡፡

በሥራ ዕድል ፈጠራ በኩል 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን ለዚህ ስኬት የግሉ ዘርፍ አስተዋጽኦ የላቀ ነበር ተብሏል፡፡

ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም እንዳሉት የአገሪቱን ሰላምና ደህነት ለማስጠበቅ የተሰራው ሥራ አመርቂ ቢሆንም በፀረ ሰላም ኃይሎች በየቦታው ተከስተው የነበሩ  ግጭቶች ተግዳሮት ነበሩ፡፡

በመተከል የተፈጸመው ጥቃትም ለዚህ ማሳያ መሆን እንደሚችል ነው የጠቆሙት።

እንደ እሳቸው ማብራሪያ በአገሪቱ የህግ የበላይነትን የማስከበር ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን ለዚህ ስኬት ደግሞ የህብረተሰቡና የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊሶች እገዛ ከፍተኛ ነበር፡፡

በአገሪቱ በአምስት ክልሎች፣ 43 ወረዳዎችና 22 ዞኖች የተከሰተውን የተፈጥሮ አደጋ በተመለከተ በተሰጠው ፈጣን ምላሸም የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ተችሏል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ በተደረገው "ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክቶች ላይ ሁሉም ዜጋ እንዲሳተፍ ጥሪ የቀረበ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ የአገሪቱን የቱሪስት መዳረሻዎች ለማስፋት፣ ኢኮኖሚውንና የሥራ ዕድል ፈጠራውን ለማሳደግ እንደሚያግዙ አስረድተዋል፡፡

ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ 3 ቢሊዮን ብር የሚያስፈልግ በመሆኑ ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ተጠይቋል፡፡

ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመክፈትና ምርጫ ለማከናወን በቀረበው ምክረ ሀሳብ መግባባት ላይ እንደተደረሰም የፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ አመልክተዋል፡፡

በአገሪቱ የተደረገው የብር ለውጥ በከፍተኛ ጥናት የተከናወነና  ኢኮኖሚውን የሚታደግ፣ የግሽበት መጠኑን ለመቀነስ የሚረዳና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን የሚያስወገድ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የብር ለውጡን ስኬታማ ለማድረግ የህግ አስከባሪዎች በአሁኑ ወቅት የተቀናጀና የተጠናከረ ጥረት እያደረጉ እንደሆነም እንዲሁ፡፡

በአጠቃላይ መንግስት የለውጥና ህግ የማስከበር ተግባራቱን ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግ የጀመረውን ጥረት አጠናከሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊዋ ቢልለኔ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው ባለፉት ሦስት ወራት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በአዲስ አበባና በተወሰኑ የኦሮሚያ ከተሞች በተፈጠረው ሁከት የ160 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 360 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸመው ጥቃት 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ አስረድተዋል፡፡

"በድርጊቱ የተሳተፉትን አካላት ተጠያቂ ለማድረግ በተሰራው ሥራ የህግ አስከባሪዎች ቅንጅት አመርቂ ነበር" ብለዋል፡፡

የአርቲስቱን ገዳዮች ለመያዝና አጠፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የፌደራል፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ፖሊስ እንዲሁም የፌደራልና የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህጎች ጥረት ውጤታማ እንደነበር ተገልጿል፡፡

በዚሀም 2 ሺህ የሚጠጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ጉዳያቸው ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀረቡ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን ወንጀሉ የተጠናና ውስብስብ በመሆኑ ፈተና እንደሆነባቸው ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ዶክተር ጌዲዮን ተናግረዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ ተቋማቸው በለውጥ ሂደት ላይ ቢሆንም የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚችለው ልክ እየሰራ ይገኛል፡፡

ተቋሙ ያለው ሃብት ወስን መሆን፣ እለታዊ ሥራዎች መብዛታቸውና ሽግግር ላይ መሆናቸው ሥራውን እንዳከበደባቸውም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም