ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ፍላጎት አላት- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

516

 አዲስ አበባ  መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥልና ውጤት እንዲያመጣ ፍላጎት እንዳላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ ማብራሪያቸው እንደተናገሩት የህዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት ጉዳይ እንጂ የማንም አገር የጸጥታ ጉዳይ ሊሆን አይችልም።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ከግብጽና ሱዳን ጋር የጀመረችው ድርድር በውጤት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ፍላጎት አንዳላትም ነው የገለጹት።

ይሁንና የሶስቱ አገሮች ድርድር የሚቋረጠው በኢትዮጵያ ሳይሆን በሌሎቹ አገሮች ምክንያት መሆኑን ነው ያነሱት አምባሳደር ዲና።

በሳምንቱ የተከናወኑ ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ስራዎችን ያብራሩት አምባሳደር ዲና በተለይ በኮቪድ 19 ምክንያት በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙና ለችግር የተጋለጡ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።

ዜጎችን ወደ አገር የመመለሱን ስራ ውጤታማ እንዲሆን አለም አቀፉ የፍልሰት ተቋም ድጋፍ ማድረጉንም አምባሳደሩ አብራርተዋል።

በሳምንቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩንና ሚኒስትር ዴኤታዎቹ ከተለያዩ ተቋማት አመራሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላትን ድፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑም በማብራሪያው ተነስቷል።

”አኖካ” ከተባለው የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ማህበር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያበከረተላቸውን ሽልማት በመጪው ህዳር ወር በአዲስ አበባ በሚካሄድ ስነ-ስርዓት እንደሚረከቡም አምባሳደር ዲና አመልክተዋል።

“አኖካ” 54ቱ የአፍሪካ አገሮችን በአባልነት የያዘ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ሲሆን በመጪው ህዳር ወር አመታዊ ስብሰባውን በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ ይጠበቃል።