የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ መጀመር ለዘርፉ እድገት ወሳኝ ነው

92

ቢሾፍቱ፣ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በመንግስት እውቅና አግኝቶ ስራ መጀመሩ ለዘርፉ እድገት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በመገናኛ ብዙሃንና ማስታወቂያ ዘርፍ  መሪ እቅድ ዙሪያ ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ  በመከረው መድረክ እንደተመለከተው ባለስልጣኑ ለሀገራዊ እድገት አስተዋፅኦ የሚያደርግ፣ ጥራቱ የተጠበቀ፣ ተደራሽ፣ በኃላፊነት ስሜት የሚንቀሳቀስና ነጻነቱ የተረጋገጠ የመገናኛ ብዙሃን እንዲስፋፋ ፣ የዘርፉን  አቅም የመገንባትና የመቆጣጠር ተልእኮን አንግቦ የተቋቋመ መንግስታዊ ተቋም ነው።

ከባለስልጣኑ የስራ ዘመን እና የሀገሪቷ የመገናኛ ብዙሃን ያሉበት የጥራትና ተደራሽነት ደረጃ ሲገመገም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት ተወስቷል።

ዘርፉ በጥራትም ሆነ ተደራሽነቱ የሚፈለገውን ያህል አለመስፋፋቱ፣ የህትመት ሚዲያውን አንቆ የያዘው ተግዳሮት አለመፈታቱ፣ በባለስልጣኑ ለመገናኛ ብዙሃን ሊደረጉ ከሚገባቸው ድጋፎች መካከል በስልጠና ብቻ ተገድቦ መቆየቱ  አሁንም ችግሮቹ እንዳልተላቀቁም ተገልጿል።

ከጎረቤት  ኬንያ ጀምሮ የብዙ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው መገናኛ ብዙሃን የራሳቸው ምክር ቤት በማቋቋምና በእሱ በመመራት ለዘርፉ ማደግ  ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አስገኝቶላቸዋል።

የብሮድካስት ባለስልጣን ከፍተኛ አማካሪ አቶ ግዛው ተስፋዬ  በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ከሌላው ዓለም ለመወዳደርና ሙያው እንዲያድግ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በወጣው ፖሊሲና ህጎች በመታገዝ  የመገናኛ ብዙሃን  ምክር ቤት  በሚመለከተው የመንግስት አካል እውቅና አግኝቶ ወደ ስራ ገብቷል።

ይሄም ዘርፉ ራሱን በራሱ እንዲመራ የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል።

መሰል የሙያ ምክር ቤቶች ባለመኖራቸው የባለስልጣኑና የሚዲያዎች ግንኙነት የአዛዥ ታዛዥ ሆኖ እንደቆየ የገለጹት ደግሞ የፋና ብሮድካስቲንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ናቸው።

አሁን የምክር ቤቱ  ወደ ስራ መግባት  የትብብር መንፈሱን እንደሚያሳድግው ተናግረዋል።

የአዋሽ ኤፍኤም ዋና ዳይረክተር አቶ በቀለ አመነ በበኩላቸው በተለይም የመገናኛ ብዙሃን  ቁጥጥሩ እርስ በርስ ከሆነ ጋዜጠኛውን ከእንግልትና የዘርፉ ተቋማትም ከፍርድ ቤት ምልልስ ነጻ በማድረግ  ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በመንግስት እውቅና አግኝቶ ስራ መጀመሩ ለዘርፉ እድገት ወሳኝ መሆኑን በምክክር መድረኩ ተመልከቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም