ፌዴራል ፖሊስ ከመስከረም 25 በኋላ “ህጋዊ መንግስት የለም” በሚል ትርምስ ለመፍጠር የሚጥሩ ሃይሎችን እንደማይታገስ ገለጸ

534

አዲስ አበባ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከመስከረም 25 በኋላ “ህጋዊ መንግስት የለም” በሚል አገራዊ ትርምስ ለመፍጠር በሚሰሩ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ የደመራና የኢሬቻ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወኑ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም አስታውቋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው በሰጡት መግለጫ ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ “ህጋዊ መንግስት የለም” በሚል አገራዊ ትርምስ ለመፍጠር በሚሰሩ አካላት ላይ የፀጥታ ሃይሉ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነው ብለዋል።

የአገሪቷን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ትርምስ ለሚፈጥሩ አካላት አንታገስም ብለዋል።

በዚህ ሁኔታ ላይ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሞክሩ ወንጀለኞች ሲያጋጥሙ ማህበረሰቡ ለፖሊስ የተለመደ ጥቆማውን እንዲያደርግና በጋራም እንዲከላከል ጠይቀዋል።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው በመስቀል የደመራና ኢሬቻ በዓላት በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በሰላም እንዲከበር ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የሚከበረው የደመራ እና ኢሬቻ በዓላትም ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከናወን የጸጥታ መዋቅሩ በቂ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ መግቢያ በሮች በሱልልታ፣ ለገጣፎ፣ ቡራዩ፣ ገላንና ሰበታ ፍተሻ እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

በበዓሉ ለመታደም የሚመጡ ምዕመናንና እንግዶችም የይለፍ ባጅ ማድርጋቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የበዓሉን እንቅስቃሴ ለማደፍረስ ዕቅድ ያላቸው ሃይሎች እንዳሉ ደርሰንበታል ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ ወደ ወንጀል ድርጊት የሚገቡ ካሉ ግን አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን ብለዋል።

በበአሉ አከባበር ወቅት ህብረተሰቡ ለየት ያለ እንቅስቃሴ ሲመለከት የተለመደ ትብብርንና ጥቆማውን ለፖሊስ እንዲያደርስ ጠይቀዋል።