ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ግንባታ ለተሳተፉ አካላት የእራት ግብዣ አደረጉ

528

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2013 ( ኢዜአ) ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ግንባታ ላይ ለተሳተፉ አካላት የምስጋና የእራት ግብዣ አድርገዋል።

ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ለመሩ ፣ ላስተባበሩ እንዲሁም የግንባታው ሂደት ላይ ለተሳተፉ አካላት የምስጋና የእራት ግብዣ መደረጉ ታውቋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት ለሌሎች ፕሮጀክቶች ልምድ እና ተሞክሮ የሚሆን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባ አዳነች በተለየ ፍጥነት እና ብርታት ፕሮጀክቱ በተባለው ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ላስቻሉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የፕሮጀክቱ ቀሪ የማጠናቀቂያ ስራዎችም በተጀመረው ፍጥነት እና ጥራት እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል ወይዘሮ አዳነች፡፡

በምስጋና የእራት ግብዣ መርሃ ግብሩ ላይ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ፣ የፕሮጀክቱ አስፈጻሚ አካላት እንዲሁም፣ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም በፕሮጀክቱ ላይ በተለያየ ሙያ የተሳተፉ የግንባታ ባለሙያዎች መታደማቸውን ከከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።