የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ገበታ ለሃገር ፕሮጀክቶች የወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ወሰኑ

59

ጋምቤላ መስከረም 14/2013(ኢዜአ) የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ለገበታ ለሃገር የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲውል የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ወሰኑ ።

አመራሮቹ የወሰኑት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ባካሄዱት ስብሰባ ነው።

የክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጀሉ በመድረኩ  አመራሩ የአንድ ወር ደመወዙን ለመስጠት  የወሰነው ፕሮጀክቶቹ ለተጀመራው ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ የላቀ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ ነው ብለዋል።

በልማት ፕሮጀክቶች  የእራሳቸውን አሻራ ለማስቀመጥ በማሰብ ጭምር የወር ደመወዛቸውን ለመለገስ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ መወሰናቸውን አስታውቀዋል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድጋፍ  ጨምሮ የተጀመረው የህዝብ ተሳትፎ ሌሎች ሀገራዊ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ከሚፈጥረው ተነሳሽነት በተጨማሪ የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ረገድም የጎላ ፋይዳ እንደለው ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ድጋፍ እንዲውል በክልሉ በአመራሮች የተጀመረው የሀብት ማሰባሰብ መረሃ ግብር በመንግስት ሰራተኞችና ሌላውን ማህበረሰብ ክፍሎች ተጠናከሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል ።

በመድረኩ ከተሳተፉ  አመራሮች መካከል አቶ ኮይት ሉዑል በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቶች ለሀገር ገጽታና ለቱሪዝም ዘርፉ የላቀ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመስጠት መወሰናቸውን ተናግረዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ድጋፍ በማድረጋቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው የገለጹት ደግሞ አቶ ኡማድ ተፋለ ናቸው።

የጋምቤላ ክልል ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ ያለበት በመሆኑ በቀጣይ ተመሳሳይ የልማት ፕሮጀክቶች ለቀየሱ ስለሚችል ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የክልሉ ከፍተኛ አመራር የአንድ ወር ደመወዙን የለገሰው በስድስት ወር ተከፍሎ የሚጠናቀቀ እንደሆነም በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም