ህገ መንግስቱን በጣሰ መልኩ በሃይል ፍላጎቴን አሳካለሁ በሚል የትኛውም አካል ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን--ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ

236

አዲስ አበባ መስከረም 14/2013(ኢዜአ)"ህገ-መንግስቱን በጣሰ መልኩ በኃይል ፍላጎቴን አሳካለሁ በሚል ማንኛውም አካል ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን" ሲሉ በኢፌዴሪ መከላከያ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹምና የኦፕሬሽናል ጉዳዮች ኃላፊ ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ የብር ኖት መቀየርን ተከትሎ ሰራዊቱ በህገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውር ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ላይ ሲውል የነበረው "የአብዮታዊ ሰራዊት መገንቢያ ሰነድ" ሰራዊቱን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ እንዳላደረገው አስታውሰዋል።  

በአገራዊ ሪፎርሙ አዲስ የሰራዊት መገንቢያ ሰነድ አገልግሎት ላይ መዋሉን ጠቁመው፤ "አሁን ላይ ሰራዊቱ ያለ ምንም ፖለቲካ ወገንተኝነት ህዝብንና የሀገርን ህልውና እየጠበቀ ይገኛል" ብለዋል።

በመሆኑም ሰራዊቱ "የማንም ፖለቲካ ፓርቲ መጠቀሚያ አይደለም፤ በየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲና አክቲቪስት ጫጫታ ከተልዕኮው አይደናቀፍም" ሲሉም ነው ያስረዱት።

ሰራዊቱ ጠንካራ ውስጣዊ አደረጃጀት እንዳለው በመጠቆም።

"ከዚህ አንጻር ፖለቲከኞች በየትኛውም የፖለቲካ ቅስቀሳቸው ላይ የመከላከያ ሰራዊቱን የሚመለከት አጀንዳ ማራመድ የለባቸውም" ብለዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተራዘመው አገራዊ ምርጫ አጠቃላይ ሂደት ህገ-መንግስቱን የተከተለ መሆኑንም ጀኔራል ብርሃኑ አብራርተዋል።

"በህገ መንግስቱ መሰረት ስልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ እንጂ 'ሽግግርና ባለአደራ' በሚል ትርምስ አይደለም" ሲሉም ነው የተናገሩት።

ከዚህ አንጻር ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለምና እንደፈለኩ እሆናለሁ የሚል አካሄድ ህገ-ወጥ መሆኑንም ገልጸዋል።

ህገ-መንግስቱን በጣሰ መልኩ 'በሃይል ፍላጎቴን' አሳካለሁ በሚል የትኛውም አካል ላይ ሰራዊቱ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም ገልጸዋል።

ጀኔራል ብርሃኑ አክለውም፤ የኢትዮጵያ የብር ኖት መቀየርን ተከትሎ ሰራዊቱ በህገ-ወጥ ገንዘቦች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ጠንካራ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ነገር ግን ሰራዊቱ ህገ-ወጥ በሚል ሰበብ ገንዘብ እየነጠቀ እንዲወስድ ፈቃድ ተሰጥቶታል በሚል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ አካላት እንዳሉም ነው የገለጹት።

ሰራዊቱ ከተገነባበት እሴት ይህን እንዲያደርግ ፈጽሞ አይፈቅድለትም ብለዋል።

በህገ-ወጥ መልኩ ሲዘዋዋር የተያዘ ገንዘብ በአንድ ቋት ተሰብስቦ የጸጥታ መዋቅሩን ለማጠናከር እንደሚውል በማብራራት።

ሆነ ብለው በተደራጀ መልኩ የሀገር ኩራት የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ስም ጥላሸት የሚቀቡ አካላት እንዳሉም ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ከውስጥ ምንጭ አገኘነው በሚል ሰበብ የመከላከያ ሰራዊት ስም የሚያጠፉ ጽሁፎችን ያሳተሙ ግለሰቦች መኖራቸውን ለአብነት አንስተዋል።

ድርጊቱ ከባድ ወንጀል ቢሆንም በትዕግስት መታለፉን ጠቅሰው፤ ከዚህ በኋላ በመሰል ተግባር የሚሳተፉ ማናቸውንም አይነት ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቀቀዋል።

ሰራዊቱ በአሁን ወቅት ማናቸውንም አይነት ተልዕኮዎችን በብቃት ማከናወን በሚያስችል ሙሉ ቁመና ላይ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም