የደቡብ ክልል በአፋር በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስና ገንዘብ ድጋፍ አደረገ

129

ሠመራ መስከረም 14/2013 (ኢዜአ) - የደቡብ ክልላዊ መንግሥት በአፋር ክልል ጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን የሰጡት በአፋር መንፈሣዊ መሪ ሡልጣን ሐንፍሬ ዓሊሚራህ ሕልፈተ-ሕይወት ሀዘናቸውን ለመግለጽና አጋርነታቸውን ለማሳየት ልዑካናቸውን በመምራት ዛሬ ሠመራ የገቡት የደቡብ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ናቸው።

አቶ ርስቱ ድጋፉን ሲያስረክቡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከአፋር ክልላዊ መንግሥትና ሕዝብ ጎን መሆናቸውን ለማሳየት መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በሡልጣን ሐንፍሬ ዓሊሚራህ ሕልፈተ-ሕይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ሥም ገልጸዋል።

በጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እንዲውል  ሁለት ሚሊዮን ብር የሚገመት ምግብ ነክ ቁሳቁስና ሦስት ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ አበርክተዋል።


ድጋፉን የተረከቡት የአፋር ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ  መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው በክልሉ በተከሰተው ጎርፍ የተገዱ ወገኖችን ለመታደግ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ድጋፍና አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን አውስተዋል።


የደቡብ ክልል ከዚህ በፊት ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ዛሬ ልዑካኑ በአካል ተገኝቶ በሡልጣን ሐንፍሬ ዓሊሚራህ ሕልፈተ-ሕይወት ሀዘኑን ለመግለጽና ጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች አጋርነቱን ለማሳየት በመምጣት ላደረገው ድጋፍ በአፋር ክልላዊ መንግሥትና ሕዝብ ሥም ምሥጋናቸውን አቅረበዋል። 

ለልዑካኑ አባላትም የተለያዩ ሥጦታዎች ተበርክቶላቸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም