በሲዳማ ክልል ጎርፍ ጉዳት ያደረሰባቸው ወገኖችን ለመርዳት ጥረት እየተደረገ ነው

71

ሀዋሳ መስከረም 14/2013 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተ ጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ። 

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ  ጎርፍ ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል በሎኮ አባያ ወረዳና ሀዋሳ ሃይቅ ዙሪያ በመስክ ተመልክተዋል።

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዘንድሮ የጣለው ከባድ ዝናብ ተከትሎ የሀዋሳ ሃይቅ ሞልቶ በመፍሰስ በአካባቢው የሚኖሩ የሰዎችን አፈናቅሏል።

በሎኮ አባያ ወረዳም ብላቴ ወንዝ አቅጣጫውን በመሳት አካባቢውን በማጥለቅለቁ ብዛት ያላቸው  ነዋሪዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዳፈናቀለም  ጠቅሰዋል።

ይህንን ተከትሎ በጎርፍ የተጎዱ ወገኖቻችንን በማየት ለመደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከነዋሪዎች ጋር ለመምከር  የመስክ ምልከታ ማድርጋቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ጎርፉ የሰው ሕይወት ባያጠፋም ማፈናቀልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አስረድተዋል።

ለደረሰው ጉዳት የሰብአዊ ድጋፍ ለማድርግ በአሁኑ ወቅት የክልሉ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም፣ቀይ መስቀል ማህበርና የፌዴራል መንግስት ትብብር ዕርዳታ እየገባ መሆኑንን አመላክተዋል።

የሁሉም አካላት ቅንጅት ባካተተ መልኩ ርብርብ እየተደረገ በመሆኑ የከፋ ችግር እንዳልደረሰ የገለጹት አቶ ደስታ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት በቀጣይ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የክልሉ የአደጋ ሥጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ አበራ ቢላ በበኩላቸው ወንዞችና ጅረቶች ሞልተው ባስከተሉት ጎርፍ  በሎኮ አባያና ወንዶ ገነት ወረዳዎች እንዲሁም በሀዋሳ ሃይቅ ተፋሰስ በሚገኙ 13 ቀበሌዎች ውስጥ  በቁጥር 30ሺህ የሚደርሱ ነዋሪዎች ለችግር መጋለጣቸውን አስታውቀዋል።

ለተጎጂዎቹ በተለያዩ አካላት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።  

ሰብአዊ ድጋፍ ለተጎጂዎቹ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ የቅድመ መኸር ምርት ግምገማ በማካሄድ በተያዘው  ወር መጨረሻ ላይ በሰብል ላይ የደረሰው ጉዳት በጥናት እንደሚለይ አስረድተዋል።

በሎኮ አባያ ወረዳ የአባያ ዙሪያ ቀበሌ ነዋሪ ከፊል አርብቶ አደር አሰፋ ሆራቶ በሰጡት አስተያየት ብላቴ ወንዝና አባያ ሃይቅ ከመጠን በላይ ሞልተው የእርሻ ማሳቸውን በማጥለቅለቁ በሰብል ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

የእርሻ ማሳቸውም በመጥለቅለቁ በቀጣይ አትክልት ለማልማት የነበራቸውን እቅድ ተደናቅፎ ጫና እንዳደረሰባቸው  ገልጸው መንግስት ወንዙ የሚገደብበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጠይቀዋል።

ሌላኛው የቀበሌው ነዋሪ  ወጣት ዮሐንስ በኬካ በበኩሉ ጎርፉ በመኸር ወቅት በሁለት ሄክታር ማሳው ላይ ያለማው በቆሎ፣ ቃሪያና ሽንኩርት  ከጥቅም ውጭ ከመሆኑ ባለፈ ከመኖሪያው ተፈናቅሎ በችግር ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም