የሱዳን ሉኡካን አባላት ጎርጎራን ጎበኙ

62

ጎንደር መስከረም 14/2013 (ኢዜአ) 22 አባላት ያሉት የሱዳን ባለሃብቶች ሉኡካን በገበታ ለሃገር ፕሮጀክት የተመረጠውን የጎርጎራ ከተማ ዛሬ ጎበኙ።

የሉኡካኑ መሪ ሚስተር ኡመር አልጋብ በጉብኝቱ ወቅት በአካባቢው አስተዳደር፣ በህዝቡ አቀባበልና መስተንግዶ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የሱዳን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውና በእነዚህ መስኮችም   ስራ ለመጀመር መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

በተረከቧቸው ኢንቨስትመንት ቦታዎችም በፍጥነት ወደ ግንባታ በመግባት በአጭር ጊዜ አጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚያበቁም አስታውቀዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ኃይለማርያም በበኩላቸው አስተዳደሩ በጎርጎራ አካባቢ ለመዝናኛ ሎጂ ግንባታ የሚውል አስር  ሄክታር መሬት ለሱዳን ባለሃብቶች ለማስረከብ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የጎርጎራ አካባቢ ለሆቴልና ቱሪዝም፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ መስኖ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ንብ ማነብ፣ ማዕድን ውሃና ለዓሳ ማቀነባበር ኢንቨስትመንት ምቹ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህንን ሀብት አቅም ባላቸው ባለሃብቶች እንዲለማ በማድረግ የአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን  በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

 የሱዳን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ዘጠኝ  የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ ናቸው።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም ሁለቱ በአማራ ክልል በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክና በጎርጎራ ሆቴልና ቱሪዝም የሚከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ሳንቃ በር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ዘመናዊ የቱሪስት መዳረሻ ሎጂ ለመገንባት ቦታ መረከባቸውንም አስታውቀዋል።

ግንባታውን በመጪው ጥቅምት ወር በመጀመር  መጋቢት ወር 2013 ዓ.ም  በማጠናቀቅ ወደ ስራ እንደሚገቡ የሚጠበቅ መሆኑን አመልክተዋል።

የሱዳን ልኡካን  አባላት በጎንደርና አካባቢው የሦስት ቀናት ቆይታ በማድረግ ልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የተመለከተ ሲሆን ወደ ባህር ዳር ከተማ እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም