የአንበጣ መንጋን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው- ግብርና ሚኒስቴር

66

ደሴ መስከረም 14/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ በመኸሩ በለማ ሰብል ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ገለጸ። 

የአንበጣ መንጋ መከላከል በሚቻልበት ዙሪያ በኮምቦልቻ ከተማ   ከባለድሻ አካላት ጋር  ውይይት።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን  በውይይት መድረኩ እንደገለጹት በሀገሪቱ በተለያየ አካባቢዎች ወጣ ገባ በማለት የሚታየው የአንበጣ መንጋ በምርት ላይ ጫና እንዳያሳድር አስግቷል፡፡

ከሰሞኑ በአፋር ክልል 26 ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ወደ አጎራባች አማራና ትግራይ የመስፋፋት አዝማሚያ  መስተዋሉን ጠቅሰዋል።

የአንበጣ መንጋው በመኸሩ ወቅት በለማው ሰብል ላይ ጉዳት በማድረስ የምርት መቀነስ እንዳይከሰት አርሶ አደሩን በማሳተፍ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

 በቂ ኬሚካል ግዥ በመፈፀም ወደ ክልሎች በማሰራጨት ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኬሚካል ርጭቱም በአራት አውሮፕላኖች ጭምር ታግዞ እየተከናወኑ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

የአንበጣ መንጋውን በ15 ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከቀጠናው ለማጥፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፋር ክልል እንሰሳት፤ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ሁሴን በበኩላቸው የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በእንሰሳት መኖና ሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በ2012/2013 የምርት ዘመን አንድም መሬት ጾም እንዳያድር ታቅዶ ከሌላው ጊዜ በተለየ በሰብል በዘር  መሸፈኑን ያወሱት ኃላፊው ፤ የታቀደውን ምርት ለማግኘት የመከላከል ስራው በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተለይ ከአዋሳኝ አማራና ትግራይ ክልሎች ጋር ህብረተሰቡን በማሳተፍ በባህላዊና ዘመናዊ ዘዴ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ከብዛቱና ፍጥነቱ አንጻር ከፍተኛ እገዛ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

ክልሉ በጎርፍ በመጎዳቱና  አመራሩ በወቅታዊ ስራ መጠመዱ ሌላው ፈተና እንደሆነ አቶ አሊ አመልክተው  በአጎራባች ክልሎች ተስፋፍቶ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንዳያሳድር አመራሩ ስራ ተከፋፍሎ  እየሰራ እንደሚገኝ  ገልጸዋል።

የአንበጣ መንጋው ለመከላከል ከአፋር ክልል ጋር  በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መለስ መኮንን ናቸው።

ከፌደራል እስከ ወረዳ ያሉ ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጋር ተቀናጅተው አካባቢውን በማሰስ በባህላዊ መንግድና ኬሚካል ርጨት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይ ምስራቅ አማራ ከፍተኛ የስጋት ቀጠና መሆኑ ተለይቶ በቂ ቁሳቁስና ኬሚካል እየቀረበ ነው ያሉት ዶክተር መለስ ህብረተሰቡ ሳይሰለች በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ ትናንት በተካሄደው ውይይት ከፌደራል፤ አፋርና አማራ ክልል የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም