የጃፓን መንግስት በሃዲያ ዞን ለሚገነባው የአዳሪ ትምህርት ቤት የ4 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ

144

አዲስ አበባ መስከረም 13/2013(ኢዜአ)የጃፓን መንግስት በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ለሚገነባው የአዳሪ ትምህርት ቤት የሚውል የ4 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ። 

ድጋፉን በዛሬው እለት በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደርና የሃድያ የልማት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ አባልና የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጋር ውል ተፈራረመዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ማቱሳንጋ ዲያሱኪ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል የሚሰሩ የተለያዩ የልማት ስራዎች ያግዛል።

በዛሬው እለት የተደረገው ድጋፍ በአካባቢው የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው ብለዋል።

ጃፓን በኢትዮጵያ በትምህርት፣ በጤናና ሌሎች ዘርፎች የተለያዩ ስራዎች በመስራት ላይ እንደምትገኝ አምባሳደሩ ገልጸዋል።

የሀዲያ የልማት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ አባልና የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሃብታሙ አበበ ድጋፍ የተደረገለት ትምህርት ቤት በዞኑ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ጥሩ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች እንደሚቀበል ጠቁመዋል።

የአዳሪ ትምህርት ቤቱ መገንባት በተማሪዎች መካከል የእርስ በእርስ ፉክክር በመጨመር የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስተሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ትምህርት እያጋጠሙ ያሉ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የጃፓን መንግስት ለትምህርት እድገት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የአዳሪ ትምህርት ቤቱ በሃዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ኪዲጋሳ ቀበሌ የሚገነባ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም