ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ2012

105

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዘመናዊት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቁ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች እንዳሉት ይነገራል። በኢትዮጵያውያን መዋጮ እየተገነባ ያለው ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ኪዩ ቢክ ሜትር ውሃ የሚይዝ ሲሆን በአፍሪካ ግዙፉ ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ግድብ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የተጠናቀቀው አመት ከግድቡ ጋር በተያያዘ ከምንጊዜውም በተለየ መልኩ በኢትዮጵያና በታችኞቹ ተፋሰስ አገራት መካከል ውጥረት የታየበት ነበር። የህዳሴው ግድብ ግንባታ ለግብጽ እረፍት ነስቷት ቆይቷል። የዓለም አቀፍ የውሃ ምህንድስና ባለሙያዎች የግድቡ ግንባታ የሱዳንንም ሆነ የግብፅን የውሃ ድርሻ እንደማይጎዳ በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም የግብጽ ፖለቲካኞች ግን “ታሪካዊ መብት አለን” በማለት የቅኝ ግዛት ዘመን ሰነዶች ላይ ይጣበቃሉ። ከዚህም አለፍ ሲል የግብጽ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ ግድቡን ልትገነባ የቻለችው እ.አ.አ በ2011 ግብጽ ቀውስ ውስጥ መግባቷን እንደምቹ ሁኔታ ተጠቅማ እንጂ በፍጹም አታስበውም ነበር ሲሉ በተደጋጋሚ ይዝታሉ። ጦርነትን ጨምሮ ሁሉንም አማራጮች ለመጠቀም ዝግጁ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ።  በ2003 ዓ.ም የፕሮጀክቱ ግንባታ  ሲጀመር በወቅቱ የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት መሐመድ ሙርሲ ግብፅን የውኃ ድርሻ ጥቅሟን ለማስከበር እስከ ጦርነት ልትሄድ እንደምትችል የሚገልጽ የቀጥታ ስርጭት ውይይት ከአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ልሂቃን ጋር ማድረጋቸው ይታወሳል።

በግድቡ ዙሪያ ግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ መርሆዎችን መሰረት ያደረገ፤ ሚዛናዊና ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም ላይ ከስምምነት እንዲደርሱ ዓመታትን የፈጀ ድርድሮችን አድርገዋል። ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ቢታዩም ይህ ነው የሚባል ውጤት ላይ አልተደረሰም። በተለይ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያውያን 2012 የግድቡ ስራ ወደ ማጠናቀቅ እየተቃረበ በመምጣቱና የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት የሚከናወንበት ዓመት በመሆኑ በሶስቱ አገራት መካከል ውጥረት የነገሰበት ነበር።     

ውጤት አልባ ድርድሮች

ከስምንት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ድርድር ባሳለፍነው 2012 በወርሃ መስከረም ተካሂዶ ነበር። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም ሁለት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን ሥራ ለማስጀመር በክረምት የውኃ ሙሌት እንደምትጀምር አስታውቃለች። ይህን ተከትሎ ግብፅ በተናጠል ሰነድ በማዘጋጀት ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንድትለቅ የሚያስገድድ ሀሳብ በማቅረቧ ድርድሩ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ቀርቷል። በዚህ ወቅት ነበር ግብጽ እንደተለመደው አፈንግጣ በመውጣት በህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች በተለይም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ ያቀረበችው። ኢትዮጵያ በበኩሏ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በሦስቱ አገራት መካከል የተደረሱ ስምምነቶችን የሚያፈርስ ከመሆኑ በተጨማሪ ሦስቱ አገራት የፈረሟቸውን የትብብር ማእቀፍ ይጥሳል በማለት የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል፤ ነገር ግን ሦስተኛ ወገን ባለበት ውይይት ቢደረግ ችግር እንደሌለው አሳወቃለች። ይህንን ተከትሎም የአሜሪካ እና የዓለም ባንክ ተወዮች በተገኙበት የሶስትዮሽ ውይይቱ እንዲቀጥል ተደረገ። በኢትዮጵያ በኩል ሦስቱ አገሮች በአሜሪካ የሚያደርጉት ውይይት እንጂ ድርድር አለመሆኑን፤ የአሜሪካ ሚናም ሦስቱ አገሮች ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ ማመቻቸት መሆኑን ተገልጾ ነበር። ሆኖም አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ጥቅም ለማስከበር ስትል ለግብጽ በመወገን በኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ልታሳድር እንደምትችል ስጋታቸውን ሲገልጹ ነበር። 

የዋሽንግተን ድርድር

አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት የተሳተፉበት የሶስቱ አገራት የውሃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለአራት ዙር ውይይት አድርገዋል። ውይይቶቹ በዋናነት  በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለማዘጀት ያለመ ነበር። ይሁን እንጂ በግብጽ በኩል የውይይቱ አቅጣጫ  ከውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ወጥቶ በውሃ ድርሻ ላይ እንዲያተኩር ግፊት አደረገች፤ አሜሪካም ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት ተሸጋገረች። ከዚህም አለፍ ብሎ አሜሪካ የግብጽን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሰነድ አዘጋጅታ ሶስቱ አገራት እንዲፈርሙበት  አቀረበች። ግብጽ በሰነዱ ላይ ወዲያው ስትፈርም ኢትዮጵያና ሱዳን ግን የሰነዱን ይዘት በመቃወም ሳይፈርሙ ቀርተዋል። ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ውይይት እንደማትመለስም በይፋ አሳወቀች። ይህ ውሳኔ ለመላ ኢትዮጵያውያን እፎይታን የሰጠ ሲሆን ለግብጽ ግን የእግር እሳት ሆኖባታል።  

ኢትዮጵያ በዋሽንግተን በሚካሄደው ስብሰባ ላይ እንደማትሳተፍ ማሳወቋን ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት ባወጣው ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ "ግድቡን በውሃ የመሙላትና ሥራውን የመሞከር ሂደት በሶስቱ አገራት መካከል ስምምነት ሳይደረስ መከናወን የለበትም" ሲል ገለጸ። መግለጫውን ኢትዮጵያ እንደማትቀበለውና የውሃ ሙሌቱ ከግንባታው ጎን ለጎን በፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህ መሰረት እንደሚከናወን ምላሽ የተሰጠው ወዲያው ነበር። በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንም የአሜሪካንን መግለጫ በመቃወም የግድቡ ግንባታ ሂደት አጠናከረው እንደሚቀጥሉ ለዓለም መድረክ አሳይተዋል። 

አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ዙሪያ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ የአሜሪካ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላት፣ የሃገሪቱ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባልደረቦች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎችና የፖለቲካ ተንታኞች በሃሳብም በጽሑፍም ሞግተዋል። አሜሪካውያኑ የትራምፕ አስተዳደር ለግብጽ የሚያሳየው ውግንና አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ አጋርነት ሊያሳጣት እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።

ወደ አረብ ሊግ

የአረብ ሊግ አባል ሀገራት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያላቸው አቋም ለግብጽ የወገነ ስለመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጧቸው መግለጫዎች ይታወቃል። ግብጽ ከዋሽንግተን ድርድር በኋላ ድጋፍ ለማሰባሰብ በቀጥታ ያመራችው ወደ አረብ ሊግ አገራት ነበር። የሊጉ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በየካቲት ወር 2012 ባደረጉት ስብሰባ ግብጽ በናይል ውሃ ላይ ያላትን “ታሪካዊ መብት” እንደሚደግፉ በመግለጽ ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ ሰነድ አጽድቋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም የሊጉ አባል ሀገራት የውሳኔ ሀሳቡን ሲደግፉ፣ሱዳን ግን በግልጽ ተቃውማለች፡፡ ጅቡቲ፣ሶማሊያና ኳታርም ግድቡን በሚመለከት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መቃወማቸውን የሚያሳዩ የተለያዩ ዘገባዎች ወጥተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ በሚደረገው ድርድር ስምምነት ላይ ቢደረስም ባይደረስም በክረምት የግድቡን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ከመጀመር የሚያስቆማት ሃይል እንደሌለ በተደጋጋሚ አሳውቃለች፡፡

የጸጥታው ምክር ቤት እና ውሳኔው

የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅማ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ሙከራ አድርጋ ያልተሳካላት ግብጽ የዐባይን ወንዝ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ካላት ፍላጎት የተነሳ የህዳሴው ግድብ ጉዳይ በቀላሉ እንዲፈታ ስለማትፈልግ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እንዲሄድ ከፍተኛ ግፊት አድርጋለች።  ግብፅ ለጸጥታው ምክር ቤት ያስገባችው አቤቱታ ስልሳ ሦስት ገፅ ደብዳቤ ላይ “ለህልውናዬ አደጋ ነው” ያለቻቸውን ጉዳዮች በዝርዝር በመጥቀስ ሦስቱ አገራት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ምክር ቤቱ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቃለች። ምክር ቤቱ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ኢትዮጵያ ውሃ ከመሙላት እንድትታቀብና ጣልቃ በመግባት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ስትልም አሳስባለች። ይህም አልበቃ ቢላት በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ በመገኘት አቤቱታዋን ማስረዳት እንደምትፈልግ በደብዳቤው ላይ ገልፃለች። ይሁን እንጂ ግብጽ የሶስቱን ሀገራት የውይይትና የድርድር ሃሳብ በመተው ወደሌሎች ሀገሮችና ተቋማት መሄዷ ኢትዮጵያን ከልማቷ እንደማያስተጓጉላት በመግለጽ ግብጽ ላቀረበችው አቤቱታ ምላሽ የሚሆን ሰነድ ለጸጥታው ምክር ቤት ቀርቧል።

የጸጥታው ምክር ቤትም ብቸኛው የመፍትሔ መንገድ በባለ ጉዳዮቹ መካከል የሚደረግ ውይይት ነው በማለት በግብጽ ጥያቄ ላይ ውሃ የሚቸልስ መልስ ሰጥቷል። የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ “በእኛ በኩል ባለጉዳዮችን ለማገልገል ፍጹም ፈቃደኞች ነን" ሲሉ አክለዋል። ይህን ተከትሎ ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲካሄድ ውሳኔ በማሳለፉ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ድልን ስትቀዳጅ ግብጽ ግን ልፋቷነ ከንቱ አድርጎባታል።  

ወደ አፍሪካ ህብረት

ያሰቡትን ያህል ውጤታማ መሆን ባይችሉም የተያዘው የፈረንጆቹን አዲስ አመት መግባት ተከሎ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሀገራት መሪዎችን ድጋፍ ለማሰባሰብ በርካታ ጉዞዎችን አድርገዋል። ሚዲያዎቻቸውም በስፋት እንዲዘምቱ አድርገዋል።

ግብጽ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጀምር ከነመኖራቸውም ልታስታውሳቸው ያልቻለችውን ድሃ የአፍሪካ ሃገራትን ለማባበል ያልተሳካ ጉዞዎችን አድርጋለች። የግብጽ ልኡካን ያላዳረሱት የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት የሉም ለማለት በሚያስችል ደረጃ ተንቀሳቅሰዋል። ከአፍሪካ አገራት ደቡብ አፍሪካ፣ ቡሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ታንዛኒያ፣ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ኒጀርና ሩዋንዳን የመሳሰሉትን አነጋግረዋል። ወደ ሰሜን አፍሪካዎቹ አልጄሪያ፣ ቱኒዝያና ሞሪታንያ ያደረጉዋቸው ጉዞዎችም ያስገኙላቸው ነገር ቢኖር የስልጣን አቻዎቻቸውን ፈገግታ ብቻ ስለመሆኑ ጉዳዩን የተከታተሉ ግብጻውያን ተቺዎች በስፋት ሲያብራሩት ከርመዋል።

ከሃያላኑ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ተማጽኖን ማእከል ያደረጉት የፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲና የሳሚ ሽኩሪ ተደጋጋሚ ጉዞዎች ውጤት ሳያስገኙ ቀርተዋል። በመጨረሻም ሁሉም መንገድ ዝግ ሲሆን ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመጡ አስገድዷቸዋል።

ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር መደረጉ ለኢትዮጵያ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ስለመሆኑ የተነገረለት ሲሆን የግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቅ፣ በድርቅ ወቅት የውሃ አሞላል፣ የግድቡ አስተዳደርና ቁጥጥር፣ የግድቡ ደህንነት ጉዳዮችን በተመለከተ የሶስቱ አገራቱ የቴክኒክና የህግ ባለሙያዎች ውይይት ማድረግ ጀምረዋል። ውይይቱ ስምምነት ላይ የሚያደርስ ስለመሆኑ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካ እንዲዳኝ መደረጉ ትልቅ እምርታ መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ።  

የኢትዮጵያውያንን የአንድነትና የትብብር ማሳያ

ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአባይ ወንዝ ላይ ምንም አይነት የልማት ስራዎችን እንዳትሰራ ከፍተኛ ጫና ሲደረግባት የነበረ ሲሆን በግብጽ በኩል ጉዳዩ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው በሚል ብሂል ውዝግብ ስትፈጥር ቆይታለች። ኢትዮጵያ በ2012 የክረምት ወራት የውሃ ሙሌት እንደምታከናውንና ለዚህም የማንንም ይሁንታ እንደማትጠብቅ አስቀድማ ባሳወቀችው መሰረት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የታቀደለትን 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ያለፈው በሐምሌ ወር መያዝ ችላለች። ይህ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ ኢትዮጵያንን ከምንጊዜውም ይበልጥ ያስፈነደቀ ክስተት ሊሆን ቻለ። በተለይ ዓመቱ በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ውጥረት የታየበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ተደርጎ ተወስዷል። ክስተቱም የኢትዮጵያውያንን የአንድነትና የትብብር ጥንካሬ ማሳያ ታላቅ አርማ ስለመሆኑ ተነገረ፤ ዐባይ ወንዝም ሀይቅም ሆነ ተባለ። በአገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን በአደባባይ ከመግለጽ ባሻገር “ግድቡ የእኔ ነው” የሚሉ ዘመቻዎችም ተጠናክረው ቀጥለዋል።  የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም “ግብጽ ላለፉት ዓመታት የነበራትን የበላይነት አጣች፤ በዲፕሎማሲው ረገድ የተሸነፈች ይመስላል፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት ጀምራለች” የሚሉ ዘገባዎችን በሰፊው አስነብበዋል። በወርሃ ሃምሌ መጠናቀቂያ ”ድምፃችን ለግድባችን” በሚል መርሃ ግብር በአዲስ አበባና በሁሉም የሃገሪቱ ከተሞች እንዲሁም በውጭ አገራት ጭምር በልዩ ልዩ ደማቅ ትእይንቶች ደስታቸውን ገልጸዋል።

ባሳለፍነው አመት በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁም በመላው አለም የሚገኙ ዳያስፖራዎች ለግድቡ ከምንጊዜውም በላይ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ መግለጽ የጀመሩ ሲሆን የአረቡ ዓለም የተዛባ ግንዛቤ እንዳይዝ በተለይ በአረብኛ ቋንቋ ሲያስረዱና ሲከራከሩ እንደነበር ታይቷል። የህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ ድጋፍ የሚያደርጉ ዜጎች ቁጥር ከመጨመሩም ባሻገር ኢትዮጵያዊያን ተባብረው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መስራት እንደሚችሉ በተግባር ያሳየ ስለመሆኑም ብዙዎች ተንታኞች ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደጎን አድርገው ስለ አንዲት ሃገራቸው የሚያስቡበት፣ በያሉበት የአለም ጥግ ሁሉ የሃገራቸውን ስም በኩራት የሚያስጠራላቸው ብሎም የማሸነፍና የመቻል መንፈስን አላብሷል። የአንድ የቤተሰብ አባል የማድረግ ሃይል የተላበሰውን የግድቡን ግንባታ ከጅማሬው አንስቶ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሱት ባለቤቶቹ በቀጣይም ፍጻሜውን ለማየት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው በመቀጠል የኢትዮጵያን ከፍታ ማፋጠን ይገባል መልእክታችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም