የፍትህ አካላት ቅንጅት ዜጎች የሚሹትን የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙ ያስችላል -- ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ

163

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2013 ( ኢዜአ) የፍትሕ አካላት ወንጀልን የመከላከልና ሰብዓዊ መብት የማስከበር ተግባራትን በጋራ መፈፀም ለዜጎች የተፋጠነ ፍትህ መስጠት እንደሚያስችል ተገለጸ። 

ይህን የገለጸው የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከፍትሕ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራቱ የሕግ ማስከበር ስራው ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቀነስ ያግዛል ብሏል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ በየደረጃው ካሉ የፍትሕ አካላት ጋር በቀጣዩ 10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ላይም ተወያይቷል።

በውይይቱ ከፌዴራልና ከክልል ፖሊስ፣ ከፍርድ ቤቶች፣ ከማረሚያ ቤትና በየደረጃው ከሚገኙ የፍትሕ አካላት ጋር በመቀናጀት ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን ለመከወን ማቀዱ ተገልጿል።

ዕቅዱን ያቀረቡት የጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕግ አማካሪ የቅሬታና አቤቱታ መስተንግዶ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስክር ታሪኩ ተቋሙ ከፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱ ሕግ የማስከበር ስራውን የተሻለ እንደሚያደርገው ያምናል ብለዋል።

የፍትሕ አካላቱ የወንጀል መከላከልና የሰብዓዊ መብት ማስከበር ተግባራትን በጋራ መፈፀም ከቻሉ ዜጎች የሚፈልጉትን ፍትሕ በተፋጠነ መልኩ መስጠት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

የፍትሕ አካላት በሕግ በተሰጣቸው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ቢቀመጥም የእስካሁኑ አካሔድ ውጤታማ እንዳልነበረም ጠቅሰዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሙስናና ሌሎች ወንጀሎች መበራከት የፍትሕ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያለመወጣት ችግር መሆኑን አንስተዋል።

በዛሬው የፍትህ አካላት ውይይት የተነሳው ሌላው ጉዳይ በምስክር አቀራረብ ዙሪያ እየገጠሙ ያሉ  ችግሮችን የተመለከተ ነው።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ የክልል ጉዳዩች ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገበየሁ በምስክሮች አቀራረብ ችግሮች ሳቢያ ክሶች እንደሚቋረጡ ገልፀዋል።

ከ2010 እስከ 2012 ዓ.ም ለፍርድ ቤት ከቀረቡ የክስ መዝገቦች ከ33 ሺህ በላይ የሚሆኑት በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጠዋል።

ችግሩን ለማስወገድ የምስክሮች አድራሻ አመዘጋገብና የተከሳሽ የዋስትና አሰጣጥ ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት ተግባር መከናወን እንደሚገባም አክለዋል።

የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በየደረጃው ከሚገኙ የፍትሕ አካላት ጋር እያካሔደ ያለው ውይይት ነገም ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም