በጋምቤላ ክልል ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት በኋላ ለኮቪድ-19 መከላከል የሚደረገው ጥንቃቄ ቀንሷል ተባለ

79

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2013 ( ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የኮሮናቫይረስ  ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥንቃቄ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት በኋላ መቀዛቀዙ ተገለጸ።

በክልሉ እስካሁን ያለው የመመርመሪያ ላቦራቶሪ አንድ ብቻ ነው።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያዙም ሆነ ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ቫይረሱ እንደገባ ከመንግስትና ከጤና ሚኒስቴር የተለያዩ መመሪያዎች መውጣታቸውም የሚታወስ ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ መደረጉና የቫይረሱን ስርጭት መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ ተደርገው ነበር።

ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጠናቀቅን ተከትሎ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ይደረጉ የነበሩ ጥንቃቄዎች እየቀሩ መሆናቸውን መታዘብ ይቻላል።

የኢዜአ ሪፖርተር በጋምቤላ ክልል ተገኝታ ባደረገችው ምልከታ ከፍተኛ መዘናጋት መኖሩን አረጋግጣለች።

በከተማዋ መመልከት እንደተቻለው አብዛኛው ህብረተሰብ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አያደርግም፣ አካላዊ ርቀቱንም አይጠብቅም።

ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ያለውን የቫይረሱን ስርጭት ለማባባስ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው።

የክልሉ ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ ማስኮችን የሚጠቀሙት ወደ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሲሄዱ ብቻ ነው።

በተለይ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጠናቀቅን ተከትሎ በሽታው የለም የሚል መዘናጋት ውስጥ መግባታቸውንም ነው የተናገሩት።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉም በክልሉ መዘናጋት በመኖሩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ያለማድረግ ክፍተቶች መኖሩን ይስማማሉ፤ ሆኖም  ማስኮችን ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች እየሰራን ነው ብለዋል።

በጋምቤላ ክልል ከነዋሪዎች ባለፈ በርካታ ስደተኞች ያሉ ቢሆንም እስካሁን ያለው የኮቪድ-19 መመርመሪያ ላቦራቶሪ አንድ ብቻ በመሆኑ በቀን ከ90 ያልዘለለ ሰው ብቻ ምርመራ እንደሚደረግለት ጠቅሰዋል።

በክልሉ ምርመራው ከተጀመረ ጊዜ እስከ ትናንትና ብቻ ከ900 በላይ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ተረጋግጧል።

ክልሉ የመመርመሪያ መሳሪያ እንዲጨመርና ምርመራውን በስደተኞች መጠለያም ተደራሽ ለማድረግ ጥያቄ ቢቀርብም እስካሁን የተሰጠው ምላሽ አለመኖሩን ርዕሰ መስተዳደሩ ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ እስካሁን ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

ከዚህ ውስጥ 29 ሺህ የሚደርሱት ዜጎች ያገገሙ ሲሆን ከ1 ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም