የክልሉን የዓሣ ሃብት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማልማት የሚያስችል የሶስት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

101

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2013 ( ኢዜአ) የጋምቤላን ክልል የዓሣ ሃብት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማልማት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲን የዓሣ ልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነውም ተብሏል።

ወንዞች፣ ሐይቆችና ግድቦች በጋምቤላ ክልል ከሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

ይሁንና እነዚህን የተፈጥሮ ሃብቶች በዘመናዊ መልኩ መጠቀም ባለመቻሉ ለክልሉ ነዋሪዎችና ለአገር ኢኮኖሚም የሚፈለገውን አስተዋጽኦ ማበርከት አልቻለም።

በመሆኑም መንግስት በክልሉ ያለውን እምቅ የዓሣ ሃብት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማልማት የሚቻልበትን ሁኔታ ለሁለት ዓመታት ጥናት ማካሄዱ ተነግሯል።

በጥናቱም የዓሣ ሃብቱ በቴክኖሎጂ ታግዞ ማልማት ከቻለ ለአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለውጭ ምንዛሬና የአገሪቷን የዓሣ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል ተለይቷል።

ጥናቱን እውን ለማድረግም ክልሉ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂና ከግብርና ሚኒስቴሮችና ከጋምቤላ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን ለሶስት ዓመታት የሚተገበር የዓሣ ሃብት ልማት ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።

ፕሮጀክቱ ለአምስት ሺህ የክልሉ ወጣቶች የስራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተነግሯል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ  ፕሮጀክቱ  ለበርካታ  ወጣቶችና ሴቶች በርካታ  የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሲን በላይም የፕሮጀክቱ ይፋ መሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የዓሣ ምርት ፍላጎት ለማሟላት ይረዳል ነው ያሉት።

በክልሉ የሚመረተው አሳ ከውጭ በከፍተኛ ምንዛሬ ከሚገባው አሳ በጥራት የማያንስ በመሆኑ የክልሉ ምርት ተወዳዳሪ ማቅረብ  ።

መንግስት በቴክኖሎጂ ተደግፈው ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ዘርፎች የእንስሳትና ዓሣ ሃብት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ ናቸው።

በክልሉ እምቅ የዓሣ ሃብት ቢኖርም በኋላ ቀር ዘዴ የሚወጣ በመሆኑ በሃብቱ መጠቀም አለመቻሉን አንስተዋል።

በመሆኑም በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ሃብቱን ለማልማት ፕሮጀክቱ እንዲጀመር መደረጉን ነው የተናገሩት።

ለሶስት ዓመታት በሚተገበረው ፕሮጀክት ስድስት የዓሣ ማስፈልፈያ፣ ማከማቻና ማሰራጫ ማዕከላት ይገነባሉ ነው የተባለው።

በአገርአቀፍ ደረጃ እየተቀየረ የመጣውን የፕሮጀክት አፈጻጸም ተሞክሮ በመውሰድ የዓሣ ሃብቱን በተያዘለት ጊዜ በማልማት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም የስራ ሃላፊዎቹ አረጋግጠዋል።

እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ ፕሮጀክቱ የዓሣ ሃብት ላላቸው ሌሎች ክልሎች ሰርቶ ማሳያ የሚሆን ነው።

በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የዓሣ ማስፈልፈያና ማባዣ ማዕከል በመገንባት ዩኒቨርሲቲውን የዓሣ ልህቀት ማዕከል ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

በማዕከሉ በዓመት እስከ 40 ሚሊዮን የዓሳ ጫጩቶች እንደሚመረቱም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

በጋምቤላ ክልል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በዓመት እስከ 17 ሺህ ቶን ዓሣ የማምረት አቅም ቢኖርም እየተመረተ ያለው ከ300 እስከ 400 ቶን ብቻ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም