የመስቀልና የእሬቻ በዓላት ሲከበሩ ከሚፈቀዱ ስነ ስርዓቶች ውጪ የሆኑ እንቅስቃሴዎች የተከለከሉ ናቸው -- የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

69

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2013 ( ኢዜአ) ''የመስቀልና የእሬቻ በዓላት ሲከበሩ ከሚፈቀዱ ስነ ስርዓቶች ውጪ የሆኑ እንቅስቃሴዎች የተከለከሉ ናቸው'' ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ህብረተሰቡ በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለመስቀልና ለእሬቻ በዓላትን ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የፖሊስ አባላት ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በቂ የጸጥታ አባላትን እንደመደበና አስፈላጊ ሎጅስቲክ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በዓላቱ ሲከበሩ ከሚፈቀዱ ስነ ስርዓቶች ውጪ የተለየ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይቻል አመልክተዋል።

የእርስ በርስ ግጭትን የሚፈጥሩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ሰላምን ለማደፍረስ በሚጥሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ነው ኮሚሽነር ጌቱ የገለጹት።

በህግ ከተፈቀደ ሰንደቅ ዓላማና አርማ ውጪ ሌሎችን በመያዝ ወደ በዓላቱ ስፍራ መምጣት የተከለከለ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፈቃድ ከተሰጠው አካል ውጪ ርችት መተኮስ እንደማይቻል ገልጸው፤ ይሄን ሲፈጽሙ በተገኙት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አመልክተዋል።

አንዳንድ አካላት በርችት መተኮስ ሽፋን ሰላምን ለማደፍረስ የሚጥሩ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

በዓላቱን የሚያስተጓጉሉ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ሁሉም አካላት ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዓላቱ በውስን ተሳታፊዎች እንደሚከበሩ አውስተው፤ በመስቀል በዓል እንዲሳተፉ ባጅ ከተዘጋጀላቸው ተሳታፊዎች ውጪ ሌላ ሰው መምጣት እንደማይችል ገልጸዋል።

የእምነቱ ተከታይ ይሄንን በመገንዘብ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በዓላቱ በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ ከጸጥታ አካላት ጋር ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ በጋራ እየሰራ መሆኑን ነው ኮሚሽነር ጌቱ የገለጹት።

የበዓላቱ ተሳታፊዎች የተለየ እንቅስቃሴ ካጋጠማቸው በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት እንዲሁም በ011-111-01-11 እና በ991 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል ማሳወቅ እንደሚችሉም ገልጸዋል።

የደመራ በዓልን አስመልክቶ የሚዘጉ መንገዶችን ለህብረተሰቡ ነገ በዝርዝር እንደሚገለጽ ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ጌቱ የመስቀልና እሬቻ በዓላት የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የደስታ እንዲሆን ተመኝተዋል።

የመስቀል በዓል ዋዜማ የደመራና የመስቀል በዓል መስከረም 16 እና 17 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲሁም የእሬቻ በዓል በአዲስ አበባ መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም ይከበራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም