ከኮቪድ-19 መከሰት በኋላ የመጀመሪያው የአትሌቶች የሠዓት ማሟያ የማጣሪያ ውድድር ተካሄደ

81

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2013 ( ኢዜአ)  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኮቪድ-19 ከተከሰተ ከወራት በኋላ የመጀመሪያውን የአትሌቶች የሠዓት ማሟያ የማጣሪያ ውድድር በሰንዳፋ ከተማ አካሄደ።

የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር በመጪው ጥቅምት በፖላንድ ጊዲኒያ ከተማ ይካሄዳል።

በዚህ የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር የሚካፈሉ አትሌቶችን ለመምረጥም ዛሬ ሰንዳፋ ላይ የሠዓት ማሟያ ማጣሪያ ውድድር ተካሂዷል።

ውድድሩ በሴቶችና በወንዶች በድምሩ 20 አትሌቶችን ብቻ በማሳተፍ ነው የተከናወነው።

እነዚህ አትሌቶች የተመረጡት ባለፈው ዓመት በአገር ውስጥና በውጭ አገር ውድድሮች በነበራቸው ውጤትና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከገባ በኋላ ያላቸውን አቅም መሰረት በማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

በዚሁ መሰረት በወንዶች የ15 ኪሎ ሜትር ማጣሪያ አትሌት ኃይለማርያም ኪሮስ በቀዳሚነት አጠናቋል።

አትሌት አንዱ ዓምላክ በልሁ ሁለተኛ፤ አምደወርቅ ዋለልኝ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።


አትሌት ብርሃኑ ለገሰ፣ ጉዬ አዶላና ልኡል ገብረስላሴ ከ3ኛ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።


በተመሳሳይ በሴቶች የ15 ኪሎ ሜትር ማጣሪያ አትሌት ያለምዘርፍ የኋላ በአንደኝነት አጠናቃለች።

አትሌት ነፃነት ጉደታ ሁለተኛ ስትሆን ዘይነባ ይመር፣ አባበል የሻነህ፣ መሰረት ጎላና መድህን ገብረስላሴ ከ3ኛ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ውድድሩን አጠናቀዋል።

የፌዴሬሽኑ የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ ለኢዜአ እንደገለጹት የሠዓት ማሟያ ማጣሪያው የተዘጋጀው የአትሌቶችን የብቃት ደረጃ ለመለየት ነው።

ውድድሩ አስፈላጊውን የኮሮናቫይረስ መከላከያ የጥንቃቄ እርምጃዎች በመከተል መካሄዱንም ገልጸዋል።

በቀጣይም አትሌቶች የሚኖራቸው ዝግጅት በአገር አቀፍ ደረጃ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚወጡ መመሪያዎችን በመከተል እንደሚሆንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም