ተቋማትና ሰራተኞች አንበጣን ለመከላከል 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

570

መቀሌ መስከረም 12 /2013 (ኢዜአ) በትግራይ ተቋማትና ሰራተኞች የአንበጣ መንጋ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራን ለማገዝ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን የክልሉ እርሻና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የፀረ ተባይ ቅድመ ማስጠንቀቀያና መከላከል ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚአብሄር አረጋዊ ለኢዜአ እንደገለጹት ድጋፉን ያደረጉት ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የሰሜን ቅርንጫፍ፣ ቢ ጂ አይ ዜድ የመቀሌ ቅርጫፍና የኢትዮ- ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን ሰራተኞች ናቸው 

ከድጋፉ ውስጥ አንድ ሚሊዮን 750 ሺህ ብሩ በወርልድ ቪዠን ኢትዮጰያ የሰሜን ቅርጫፍ የተበረከተ መሆኑን ተናግረዋል ።

ቢ ጂ አይ ዜድ መቀሌ ቅርንጫፍ ስር የሚገኘው የአፈር ለምነት አስተዳደር 650 ሺህ ብርና የኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን ሰራተኞችሞ ከደሞዛቸው ያዋጡትን 195 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል ።

በድጋፍ የተገኘው ገንዘብ በክልሉ እየተካሄደ ላለው የአንበጣ መከላከልና ቁጥጥር ስራ ቁሳቁስ ግዥ እንደሚውል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል ።