ብአዴን የአማራን ሕዝብ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅና አገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሚሰራ አስታወቀ

113
ባህርዳር ግንቦት 3/2010  ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ( ብአዴን) የራሱን የውስጠ ድርጅት ችግሮች በጥልቀት ፈትሾ በማስተካከል የአማራን ሕዝብ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅና በአገር ግንባታ ሂደት የበኩሉን ለመወጣት እንደሚሰራ አስታወቀ። ድርጅቱ ላለፉት ስድስት ቀናት ባካሄደው ኮንፈረንስ ባወጣው ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ እንዳስታወቀው የተጀመረው የጥልቅ ተሀድሶ ህዝብ፣ አገርና የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመሩን ከችግር የሚያወጣ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክቷል። በድርጅቱ መርሆዎች ላይ ግልጽነት በመፍጠርና የትግል መስመሩን በማጥራት አገራዊ አንድነት እንዲጎለብት ብአዴን የስርዓቱ አደጋዎችን በመታገል ለለውጥ በጽናት እንደሚሰራም ገልጿል። በፖለቲካል ኢኮኖሚው የበላይነት እየያዘ የመጣውንና ሕብረተሰቡን ክፉኛ እያማረረ የሚገኘውን ኪራይ ሰብሳቢነት ለመድፈቅ የድርጅቱን የቀደመ ሕዝባዊነት በማንገብና ሕዝቡን በማሳተፍ እንደሚሰራ መግለጫው አመልክቷል። ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ህገ መንግስቱ ያጎናፀፋቸው መብቶች ሳይሸራረፉ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረው እንዲኖሩና አንዳንዴ የሚከሰቱ መፈናቀሎችን ለመቀነስ ከእህትና አጋር ድርጅቶች ጋር ጠንካራ ቅንጅት በመፍጠር እንደሚሰራም አስታውቋል። እንደመግለጫው ከሆነ የፌደራል ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚፈታተኑ አስተሳሰብና ተግባራት በእርምት መቋጫ እንዲያገኙ እንደ አገር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ድርጅቱ የበኩሉን ሚና ይወጣል። ብዝሀነትን በአስተማማኝ ለማስቀጠል፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲያብብና ለሕብረትና አብሮነት የማይበጁ አስተሳሰቦች እንዲሸነፉ ለማድረግ ብአዴን በትጋት ይሰራል። ብአዴን የቀደመ ህዝባዊነቱን በማንገብ ድህነትና ኋላቀርነትን ለማሸነፍ የተጀመረውን አገራዊ ትግል የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠል የክልሉን ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ እንደሚሰራም ድርጅቱ በአቋም መግለጫው አረጋግጧል። በተለይም የሴቶችንና ወጣቶችን ማህበራዊ ችግሮች በመፍታት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ነው በመግለጫው ያብራራው። ብአዴን/ኢህአዴግ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ አቅሙን በማሳደግ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ እንዲጎለብትና ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ይበልጥ የተመቸ እንዲሆን የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግም ባወጣው የአቋም መግለጫ ላይ አስታውቋል። " የተሃድሶ ንቅናቄያችንን የበለጠ በማጥለቅ፣ በማስፋትና ቀጣይነቱን በማረጋገጥ የሕዝባችንን የለውጥ ተስፋ እናስቀጥል" በሚል መሪ ሐሳብ ከሚያዚያ 27 እስከ ግንቦት 02 ቀን 2010 ሲካሄድ የቆየው የብአዴን ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል። በኮንፈረንሱም በየደረጃው የሚገኙ የብአዴን አባላት ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል። በሌላ በኩል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን አቶ ተስፋዬ ጌታቸው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። ከእዚህ በተጨማሪ የአመልድ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር አምላኩ አስረስ የጥረት ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሹመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም