በዞኑ በሰባት ሺህ ሄክታር ላይ የተከሰተ የአንበጣ መንጋን ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው

579

ወልዲያ፣ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ ) በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ በ7 ሺህ 254 ሄክታር ግጦሽ ሣርና የሰብል ማሣ ላይ የተከሰተን አንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በጽሕፈት ቤቱ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ መለሰ መልኩ ለኢዜአ እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው ከአምስት ቀን በፊት በወረዳው በስምንት ቀበሌዎች ተከስቷል።

የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሩን በማሳተፍ የአንበጣ መንጋውን በባህላዊና ዘመናዊ መንገድ ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን በተካሄደ የቁጥጥር ሥራ 501 ሄክታር የሰብል ማሣና የግጦሽ ሣር ከአንበጣ መንጋው ነፃ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በቁጥጥር ሥራው ከ500 ሊትር በላይ ኬሚካል ተረጭቶ ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።

ቀሪውን 6 ሺህ 753 ሄክታር ግጦሽ ሣርና የሰብል ማሣ ከመንጋው ነፃ ለማድረግ የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

በወረዳው የቀበሌ 023 ነዋሪ አርሶ አደር ሁሴን ይመር የአንበጣ መንጋን ከአካባቢው ለማባረር እየተደረገ ባለው ጥረት እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

“መንጋው ከፍተኛ ቁጥር ያለው በመሆኑ በቀላሉ መከላከል አዳጋች ሆኗል” ያሉት አርሶ አደር ሁሴን ኅብረተሰቡ በመተባበር ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

“ከአምስት ቀን ጀምሮ በጭፍጨፋና ኬሚካል በመርጨት መንጋውን ለማባረር እየጣርን ነው” ያሉት ደግሞ

የቀበሌ 024 ነዋሪ አርሶ አደር መንገሻ ተስፋዬ ናቸው።