በአፋር ክልል ከ35 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ስንዴ በመስኖ ለማልማት ታቅዷል

69

መስከረም 12/2013(ኢዜአ) በአፋር ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ስንዴ በመስኖ ለማልማት ዕቅድ መያዙን የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት አስታወቀ፡፡

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ስንዴ በመስኖ ለማልማት የተያዘውን ዕቅድ ማስጀመርን በተመለከተ በሰመራ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።  

በውይይቱም የክልሉ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት፣ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ባለሃብቶች ተሳትፈዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ነኢማ መሃመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በክልሉ ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እንደሚለማ ገልጸዋል፡፡

ስንዴ ከጤፍ ማሽላና በቆሎ ቀጥሎ በኢትዮጵያ በስፋት እንደሚመረት የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፣ ዕቅዱን ወደ ሥራ በማስገባት አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ ለመቀነስ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

"ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር 5 ሺህ ሄክታር መሬት ለክልሉ ወጣቶች በመስጠትና የግብዓት ድጋፍ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋልም " ብለዋል ወይዘሮ ነኢማ፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ አሲም በበኩላቸው "በአገር አቀፍ ደረጃ 300 ሺህ ሄክታር መሬትን በማልማት የአገሪቱን የስንዴ ፍጆታ አምሳ በመቶ ለማስቀረት ይቻላል" ብለዋል፡፡

ዶክተር ፈቶ እንዳሉት የመስኖ ልማቱ በተለይ የስንዴ ምርትን በስፋት በማከናወን ከውጭ ይገባ የነበረውን ተመሳሳይ ምርት ለማስቀረት ይረዳል።

ለዕቅዱ ስኬት የሁሉም አካላት ጥረት ወሳኝ በመሆኑ የበኩላቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።

የመስኖ ልማቱ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወን ሲሆን ዱብቲ፣ አሳይታ፣ አፍምቦ፣ ገዋኔ፣ አሚባራ፣ አዋሽፈንታሌ እና ሚሌ ወረዳዎች ዕቅዱ የሚተገበርባቻው መሆኑ ተመልክቷል።

በክልሉ በግብርና ሥራ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የግብርና ሚኒስቴር የግብዓት እና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የክልሉ መንግስትም የመስኖ ልማት ስራው ውጤታማ እንዲሆን በሚችለው ሁሉ ትብብርና ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጧል፡፡

ከውይይቱ በኋላም የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት እና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ለስንዴ መስኖ ልማት የታሰበውን መሬት ጨምሮ የጎርፍ ውሃ የሞላበትን እና በአንበጣ መንጋ የተወረረውን መሬት ጎብኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም