ኢዜማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የ500 ሺህ ብር ድጋፍ አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የ500 ሺህ ብር ድጋፍ አበረከተ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የ500 ሺህ ብር ድጋፍ አበረከተ።
የገንዘብ ድጋፉ ከፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት የተሰበሰበ መሆኑ ተገልጿል።
የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊዎች በሁሉም አገራዊ ጉዳዮች ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ የፓርቲው ደጋፊዎች ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም ገልጸዋል።
ይህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊዎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፏቸውን በማጠናከር አገራዊ ሃላፊነትና ግዴታቸውንም ጭምር እንዲወጡ ለማድረግ እንደሆነ ነው የገለጹት።
በአገሪቷ የሚስተዋለው የፖለቲካ ባሕል በልዩነት ላይ ያተኮረ በመሆኑ በጋራ መሰራት በሚገባቸው አገራዊ ጉዳዮች ላይ መስራት ሳይቻል ቆይቷል ብለዋል።
የሕዳሴ ግድቡን መደገፍ ሰፊ የፖለቲካ ትርጉም ያለው በመሆኑ እንደ አገርና እንደ ፖለቲካ ማኅበረሰብ ያሉ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው በአገራዊ ጉዳዮች መተባበር እንደሚገባም ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታገል ቀኑብህ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ በተለያየ መንገድ ድጋፋቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም በአገራቸው ልማትና በሁለንተናዊ ጉዳዮች ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
ኅብረተሰቡም ግድቡ ከፍጻሜ እስኪደርስ በአንድ ዓላማ በጋራ በመሰለፍና አሻራውን በማኖር ተሳትፎውን መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የእስካሁን የግንባታ ሂደት በኅብረተሰብ ተሳትፎ ከ13 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል።