የፀረ ሙስና ትግሉን ሀገራዊና የተናበበ ለማድረግ ከክልሎች ጋር እየተሰራ ነው- ኮሚሽኑ

አዳማ መስከረም 11/2013(ኢዜአ) በሙስና ላይ የሚደረገውን ትግል ሀገራዊና የተናበበ ለማድረግ ከክልሎች ጋር የጋራ እቅድ በማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።

በእቅዱ ዙሪያ የክልሎች ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች ግልፅ ግንዛቤ ኖሯቸው ለተፈፃሚነቱ እንዲረባረቡ ለማስቻል ኮሚሽኑ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

በኮሚሽኑ የክልሎች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ መለስ ተገኝ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በሙስና ላይ የሚደረገውን ትግል ሀገራዊና የተናበበ ለማድረግ መሰራት ያስፈልጋል።

በዚህም ትግሉን ወጥነት ባለው መልኩ ለመምራት የክልሎች ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

በተለይ ከክልሎች ጋር የጋራ እቅድ አዘጋጅተናል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አጠቃላይ ሀገራዊ የትውልድ ስነ ምግባር ግንባታና የፀረ ሙስና ትግል የሚመራበት ፍኖተ ካርታ ጭምር ተሰናድቶ የጋራ ግንዛቤና አቅጣጫ በመያዝ  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የክልሎች ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የስራ ሃላፊዎችና ሙያተኞችን በእቅዱ ተፈፃሚነትና አቅጣጫ ላይ አቅም መገንባትና ማዳበር፣ግልፅ ግንዛቤ ኖሯቸው ለተፈፃሚነቱ እንዲረባረቡ ለማስቻል ያለመ መድረኩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

ውስብስብ የሆነና በኔትዎርክ የተሳሰረ የሙስና መረብ ለመበጣጠስ የተቀናጀና የተናበበ ኃይል በሁሉም የአስተዳደር እርከን መፍጠር ወሳኝ መሆኑንም  ተናግረዋል።

ከሙስናና ምዝበራ ጋር የተቆራኘ ኃይል በየጊዜው አጀንዳ በመፍጠር ሀገር እንዳትረጋጋና ለዘረፈው ንብረት ተጠያቂ ላለመሆን እየታገለ በመሆኑ የፀረ ሙስና ትግል ስልት መቀየር አለብን ብለዋል።

በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣትና የህዝቡን ፍላጎት ያማከለ ተግባር ለማከናወን የክልሎችና የፌዴራል ፀረ ሙስና ሴክተር ተቀናጅተውና ተናበው መስራት አለባቸው ያሉት ደግሞ በመድረኩ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ ሸኒቦ ናቸው።

በተያዘው የበጀት ዓመት ሀገሪቱን በፀረ ሙስና ትግል ስራዎች ከአፍሪካ አሁን ካለችብት 16ኛ ደረጃ ወደ 12ኛ ለማምጣት መታቀዱን ተናግረዋል።

በዚህም የታሰበውን ውጤት ለማምጣት የክልሎች ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች ግልፅ ግንዛቤ፣ እውቀትና ክህሎት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

"ካላወቅን መተግበር አንችልም" ያሉት አቶ ተስፋዬ እቅዱ በፌዴራል ብቻ የተንጠለጠለ እንዳይሆን እስከ ክልል ድረስ በማውረድ በጋራ ውጤታማ ለማድረግ  ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፌዴራል እስከ ክልል ያለው ዓላማ ፈፃሚና ድጋፍ ሰጪው የሰው ኃይሉ እቅዱን አውቆና አምኖበት እንዲፈፅመው ለማስቻል  እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረኩ ከኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ ሱማሌና ሐረር ክልሎች፣ እንዲሁም ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም