የኮሮናቫይረስን በመከላከል ሂደት የዩኒቨርሲቲዎች ሚና የላቀ ነበር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን በመከላከል ሂደት የዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፎና ሚና ላቅ ያለ እንደነበር የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ ።

የከፍተኛ ትምህርት ማስቀጠያ ቅድመ ዝግጅትና የኮሮናቫይረስን በመከላከል የግባራት አፈጻጸም ዙሪያ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።


በውይይቱ ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ተቋማቱ ወረርሽኙን በመካከላከል ሂደት እስካሁን የሚያኮራ ተግባር መፈፀማቸውን ጠቅሰዋል።


ዩኒቨርሲቲዎቹ በቀን ከ5 ሺህ ባላይ የኮሮና ተዋህሲ ናሙና የላብራቶሪ ምርመራ እያደረጉ ስለመሆኑም ገልጸዋል።


ከዚህ ባለፈ ዩኒቨርስቲዎቹ በለይቶ ማቆያነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል ያሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ እስካሁንም ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች ማቆየታቸውን ተናግረዋል።


የምርምር አገልግሎት በመስጠት ረገድም ከ40 በላይ ምርምሮች ተሰርተው በአለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ታትመዋል ብለዋል። 


ዩኒቨርሲቲዎቹ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ፣ አልኮልና ሳኒታይዘር፣ የሃኪሞች ጋዎንና ሌሎናች ቁሳቁሶችን በፈጠራ አበርክተዋልም ነው ያሉት።


ተቋማቱ 252 ሚሊዮን ብር ለኮሮና ወረርሽኝ ምርምርና የፈጠራ ስራዎች ወጭ ሲያደርጉ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በለይቶ ማቆያ ለተቀበሏቸው ሰዎች ወጭ ሆኗል።


በተለይ ደግሞ በቴክኖሎጂ ታግዘው የመማር ማስተማር ሂደቱን በማስቀጠል ውጤታማ ተግባራት ማከናወናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።


በውይይቱ ላይ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ልምዱን ያጋራ ሲሆን የዩኒቨርስቲው ተወካይ መሀመድ አባመጫ በጅማ ዞን ለሚገኙ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።


ጅማ ዩኒቨርሲቲ በልይቶ ማቆያነት እያገለገለ ሲሆን የመመርመርና የማከም ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነም አስታውሰዋል።


በአካባቢው ያሉ የጤና ተቋማትን በማገዝ፣ የአምቡላንስ አገልግሎት እንዲሁም መሰል ተግባራትን አከናውኗልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም