ትምህርትን እንደ መነገጃ የሚቆጥሩ የግል ትምህርት ቤቶች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የትምህርት ሚኒስቴር አስጠነቀቀ

57

አዲስ አበበሳ፣ መስከረም 10/2013(ኢዜአ) ትምህርትን እንደ መነገጃ የሚቆጥሩ የግል ትምህርት ቤቶች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የትምህርት ሚኒስቴር አስጠነቀቀ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) ሙያውን አክብረው የሚሰሩ የግል ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ሁሉ ትምህርትን እንደ ሸቀጥ የሚቆጥሩ የግል ትምህርት ቤቶችም እንደሚያጋጥማቸው ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት መንግስት የወሰነውን የነፃ ዝውውር ወደ ጎን በመተው የትምህርት ክፍያ ካልከፈላችሁ ወደ ቀጣዩ ክፍል አትዛወሩም የሚሉ የግል ትምህርት ቤቶች አሉ።

ቀድመው ሲያስከፈሉ ከነበረው የአከፋፈል ስርዓት ውጪ አዲስ የአካፋፈል ስርዓት ሲከተሉ የተገኙ እንዳሉም አንስተዋል።

በዚህ ተግባር ውስጥ የተገኙ ትምህርት ቤቶች እስከ መዘጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።

የትምህርት ቤቶቹ አስተዳደሮች ቢወስኑ እንኳ የተማሪ ወላጆች ማህበር ያልተስማማበት ክፍያም ሆነ አከፋፈል ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ የወላጅ ማህበር አባላትን ልጆቻችሁን እናባርራለን የሚል ማስፈራሪያም እያደረሱባቸው ስለመሆኑ መስማታቸውን አመልክተዋል።

በመሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች ትምህርትን እንደ ሸቀጥና ንግድ ከመቁጠር ይልቅ ዜጋን እንደሚያፈራ ተቋም ራሳቸውን ማየትና ለትምህርት ጥራት መጨነቅ እንደሚገባቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም