በአፋር ክልል ከ38ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቆላ ስንዴ ሊለማ ነው

110

ሰመራ መስከረም 9/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል ዘንድሮ ከ38ሺ ሄክታር በላይ መሬት በቆላ ስንዴ እንደሚለማ የክልሉ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ። 

የግብርና ሚኒስትርና የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድርን ጨምሮ ባለሃብቶችና የምርምር ማዕከላት የተሳተፉበት ክልላዊ የስንዴ ልማት ማስተዋወቂያ ጉባኤ ዛሬ በሰመራ ከተማ ተካሄዷል።

የኢንስቲትዩቱ  ተወካይ ዶክተር መሐመድ አባተ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ከ304ሺህ ሄክታር በላይ  በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት ይገኛል።

ከዚህ ውስጥ 167ሺህ ሄክታር ስንዴን ጨምሮ ለተለያዬ ጥራጥሬ ምርቶች ሊወል የሚችል ነው ብለዋል።

ሆኖም  በክልሉ አዋሽ ወንዝን ጨምሮ የተለያዩ የገጸና ከርሰ ምድር ውሃ  ቢኖርም  ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ባለመሰጠቱ አሁን እየለማ ያለው መሬት ከግማሸ በታች  እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህም ውስጥ ስንዴ ካለው ከፍተኛ ሙቀት ጋር ተያይዞ በክልሉ የማይታወቅና የደጋ ሰብል ተደርጎ ይወሰድ እንደነበር አውስተዋል።

ከ2001 ዓ.ም  ወዲሁ የወረር ግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት ዘጠኝ የዳቦና አንድ የማካሮኒ ስንዴ ምርጥ ዘርን በምርምር በማውጣት በክልሉ የሰንዴ ልማት ስራዎች እንዲስፋፉ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በክልሉ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደው የማስተዋወቅና ማላመድ ስራ የስንዴ ምርታማነትና አዋጭነቱ በህብረተሰቡ ዘንድ እየታመነበት በመምጣቱ ባለፈው ዓመት በተለያዩ ወረዳዎች 12ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ መልማቱን  ዶክተር መሐመድ አስረድተዋል።

ዘንድሮ ደግሞ 38ሺህ 185 ሄክታር መሬት በታችኛውና መካከለኛው አዋሽ በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ባለሃብቶች ፣ ወጣቶችንና ሌላውንም ማህበረሰብ በማሳተፍ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን  በበኩላቸው በግብርው ዘርፍ  በተለይም በስንዴና እንስሳት መኖ ልማት  ለሚሳተፉ ባለሃብቶች  የዘርና የሌለም ግብአት ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ለስራው የሚያስፈልግ የብድር አቅርቦት  ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በአፋር ክልል በስንዴ ልማት ለመሰማራት የተዘጋጀው 51 ባለሃብቶች እንደሉም ጠቁመዋል።

ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት  በተካሄደው  የስንዴ ልማት ውጤታማ  ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

አሁን የገጠመውን የኮሮ በሽታ ፣ጎርፍ እና የአንበጣ ክስተት በመቋቋም የተጀመረው የስንዴ ልማትን  አጠናክሮ ለማስቀጠል የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል

 በዋናነት ባለሃብቱ ወደ ስንዴ ልማት  ሲገባ ያላውን የገንዘብና መሳሪያ አቅም ያገናዘበና በእውቀት ላይ ተመስርቶ በቁርጠኝነት  መግባት እንደሚጠበቅበትም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም