ዘመናዊ የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ''ቴሌ ሔልዝ'' የተሰኘ ቴክኖሎጂ ይፋ ሆነ

102

አዲስ አበባ፣መስከረም 8/2013 (ኢዜአ) ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ዘመናዊ የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ''ቴሌ ሔልዝ'' የተሰኘ ቴክኖሎጂ ይፋ ሆነ።

ሳይንሳዊ መንገድን በመጠቀም ዘመናዊ የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው ቴክኖሎጂ የታካሚ ምልልስን በማሳነስ የኮቪድ-19ኝን ስጋት ይቀንሳል ነው የተባለው።

የህብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ኃይሉ ታምሩ ቴክኖሎጂው ይፋ በተደረገበት ወቅት እንዳሉት ተመላላሽ ታካሚዎች ወደ ህክምና ተቋም መምጣት ሳይጠበቅባቸው ባሉበት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

ህሙማን አገልግሎቱን  በስልክ፣ በኢሜልና በሌሎች የቴክኖሎጂ አማራጭ ውጤቶች በመጠቀም ከህክምና ባለሙያ በሚሰጣቸው መመሪያ መሰረት ወደ ሕክምና ተቋማት መምጣት ሳይጠበቅባቸው ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።

ታካሚዎች ህክምና ያደረጉላቸውን ኃኪሞች ለማግኘት የሚያጠፉትን ጊዜ እንደሚቀንስላቸውም ተገልጿል።

"ቴክኖሎጂው ተግባራዊ ሲሆን ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ተይዘው በየጊዜው ወደ ጤና ተቋም ለሚሄዱ ሕሙማን ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል" ብለዋል።

በቴክኖሎጂው የሚጠቀሙና አገልግሎቱን የሚሰጡ የጤና ተቋማትና ግለሰቦች አጠቃቀሙን በተመለከተ ተገቢውን መረጃ ማግኘት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የጤና ሚኒስቴር የሕክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ያዕቆብ ሰማን በበኩላቸው እንዳሉት ቴክኖሎጂው ለሕክምና አገልግሎቱ ከፍተኛ እገዛ አለው ።

የሕክምና ባለሙያዎችን እጥረትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የቴኖክኖሎጂው ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ነወ የገለጹት።

በአገሪቱ እስካሁን ድረስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የህክምና አገልግሎት መስጫ መመሪያ የሌለ መሆኑም  ተመልክቷል።

የቴክኖሎጂ አገልግሎቱ ቀደም ሲል በተበጣጠሰ መልኩ በአገሪቱ ይሰጥ እንደነበረም አቶ ያዕቆብ አስታውሰዋል።

ይህ ቴክኖሎጂ በሁሉም የአገሪቱ ትልልቅ ሆስፒታሎች የሚተገበር መሆኑን ገልጸው፣ "ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በተገቢው መልክ እንዲያገኝ የሚመለከታቸው አካላት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

በቀጣይ ቴክኖለጂው በአገሪቱ በሁሉም የጤና ተቋማት ተግባራዊ እንደሚደረገም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም