በትግራይ እና አማራ ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ

120

መቀሌ፣ ደሴ፣ መስከረም 8 / 2013 (ኢዜአ) በትግራይ አምስት ወረዳዎች እና በአማራ ደቡብ ወሎ ዞን ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት መብቃታቸው ተገለጸ።

የትግራይ ክልል ውሃ ሃብት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፍትዊ ግደይ ለኢዜአ እንደተናገሩት

ለአገልግሎት የበቁት ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ናቸው። 


የውሃ ፕሮጀክቶቹ ግንባታ ወጪ የሸፈኑው በክልሉ መንግስት፤ማህበራዊ ረዲኤት ትግራይ(ማረት) እና በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት/ ዩኒሴፍ/ ትብብር ነው።

ከታህሳስ መጀመሪያ እስከ ሰኔ መጨረሻ 2012 ዓ.ም ድረስ ባሉት ወራት ተገንብተው ሰሞኑን ለአገልግሎት የበቁት የውሃ ፕሮጀክቶች በአለማጣ፣ እንደርታ፣ነቅሰገ፣ ሰውሃ ሳዕስዕ እና ፅራዕ ወንበርታ ወረዳዎች ውስጥ ነው ብለዋል።


ጥልቅ ጉድጓድ በመቆፈርና ተጓዳኝ መገልገያዎች ተመቻችተውላቸው የተገነቡት  የውሃ ፕሮጀክቶቹ አምስት እንደሆኑ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ እያንዳንዳቸውም በአማካኝ ከ6ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል። 


በተጨማሪ በቀጣይም ተጠናቀው ለአገልግሎት የሚበቁት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አመልክተው ከመካከላቸውም ከ260 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በሸራሮ እና ዓብይ ዓዲ ከተሞች እየተገነቡ ያሉትን ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ እስከ 30ሺህ የሚሆን ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል።

በሰውሃ ሳዕስዕ ወረዳ የታህታይ ዝባን ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ለምለም እኑን በሰጡት አስተያየት ፤ በቀበሌያቸው የተገነባው የውሃ ተቋም ቀደም ሲል ውሃ ፍለጋ በእግር ጉዞ ለሦስት ሰዓታት ሲያደርጉት የነበረውን አድካሚ ጉዞ እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

በአካባቢቸው ተገንብቶ ለአገልግሎት የተዘጋጀው የንፀህ መጠጥ ውሃ ተቋም እንዳይበላሽ ለመጠበቅ ኮሚቴ አዋቅረው እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ በአለማጣ ወረዳ የለምለም ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሞጎስ ኃይለኪሮስ ናቸው።

በሌላ በኩል በአማራ ደቡብ ወሎ ዞን ከተሞች በተጠናቀቀው ዓመት ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን የዞኑ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የቤቶች መሰረተ ልማት ቡድን መሪ አቶ ወርቅነህ ሽፋው ለኢዜአ እንደገለጹት ከተገነቡትም መካከል 94 ኪሎ ሜትር ጠጠርና የድንጋይ ንጣፍ መንገድ፣ 42 ኪሎ ሜትር የመብራት መስመር ዝርጋታና የውሀ ማፋሰሻ ቱቦዎች ይገኙበታል።


እንዲሁም የህብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበሩ 15 የውሃ ቦኖዎች፣ አምስት መለስተኛ የአውቶቡስ መነሃሪያዎች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

ለግንባታው ከተደረገው የገንዘብ ወጪ  ውስጥ 33 ሚሊዮን ብር በህብረተሰቡ ቀሪው በመንግስትና አጋር የልማት ድርጅቶች  የተሸፈነ መሆኑን አብራርተዋል።

በሐይቅ ከተማ የቀበሌ አንድ ነዋሪ ወይዘሮ ዘሐራ አህመድ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የተሰራው የድንጋይ ንጣፍ መንገደ  ክረምት ከበጋ ይገጥማቸው ከነበረው የጭቃና አቧራ ችግር እንዳቃለላቸው ተናግረዋል።

ለስራውም በገንዘብና ጉልበታቸው የድርሻችውን እንደተወጡ ጠቁመዋል።

በኮምቦልቻ ከተማ የቀበሌ አስር ነዋሪ አቶ እሸቱ አሊ በበኩላቸው ቀበሌያቸውን ከሌላ አካባቢ ጋር በተለያየ አቅጣጫ የሚያገናኝ የጠጠር መንገድ በመገንባቱ በአቅራቢያቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

በደቡብ ወሎ በተያዘው የበጀት ዓመትም ከ115 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተለያዩ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አመልክቷል።