ኮሌጁ ማስተማሩን ካቋረጠ በኋላ ያልሰራበትን ገንዘብ ማስከፈሉ ቅሬታ ፈጥሯል

59

ሀዋሳ፣ መስከረም 8/2013 (ኢዜአ) በጉራጌ ዞን ማረቆ ወረዳ ቆሼ ከተማ ተማሪዎችን ተቀብሎ የጀመረውን የማስተማር ስራ ከቋረጠ በኋላ ያልሰራበትን ገንዘብ ማስከፈሉ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የ"ኦዳ ቢዝነስ ኮሌጅ " ተማሪዎችና ወላጆች ገለጹ።

የደቡብ ክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ በበኩሉ በማጣራት የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል።

የቅሬታ አቅራቢዎቹ ተወካይ ተማሪ አሊዬ መሐመድ ለኢዜአ እንዳለው ኮሌጁ እውቅና ተሰጥቶኛል ባለው የትምህርት መስኮች አንዱ በሆነው  በአካውንቲንግ መስክ በመመዝገብ ካለፈው ዓመት መግቢያ ጀምሮ የደረጃ አንድ ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቷል።

በወቅቱ ኮሌጁ ስራውን የጀመረው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በሂዩማን ሪሶርስ ማናጅመንትና አካውንትንግ የትምህርት መስኮች ከ200 በላይ ተማሪዎችን በመቀበል መሆኑን ጠቁሟል።

እያንዳንዱ ተማሪ ለምዝገባ 100 ብር፣ለሚማረው የትምህርት ኮርስ ደግሞ በየወሩ 300 ብር እየከፈሉ መደበኛ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ እንደነበር አውስቷል።

የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ የመማር ማስተማሩ ስራ መቋረጡ እየታወቀ ምንም ዓይነት የቤት ሥራዎች በማይሰጣቸው ሁኔታ በኮሌጁ አካላት ክፍያ እንድንፈጽም ተደርገናል ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

በኮሌጁ አሠራር ጥርጣሬ የገባቸው ተማሪዎች ሁኔታው እንዲጣራላቸው ለሚመለከተው አካል ቅሬታ ማቅረብ በጀመሩ ማግስት  የኮሌጁ አካላት ተቋሙን ዘግተው መሰወራቸውን አስረድቷል።

በዚህም ምክንያት የትምህርት ጊዜያቸው በከንቱ ከመባከኑ ባለፈ ከገንዘባቸውም ሳይሆኑ እንግልት እየደረሰባቸው  መሆኑን ገልፆ መንግስት መፍትሄ  እንዲሰጣቸው ጠይቋል።

የተማሪ ወላጆች ተወካይና የቆሼ ከተማ ነዋሪ አቶ ሙስጠፋ አህመድ በበኩላቸው እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም ወላጆች የልጃቻቸውን ተስፋ ለማየት በማስተማር ላይ እንደነበሩ ተናግረዋል።

ወርሃዊ  ክፍያውን ወረርሽኙ ከተከሰተም በኋላ  እንዳላቋረጡ አመልክተዋል።

የአንድ ዓመት ክፍያ ካጠናቀቁ በኋላ ዘንድሮ የተማሪዎች ምዝገባ ይጀምራል ብለው ሲጠባበቁ ባሉበት ሁኔታ   የኮሌጁ አካላት ከአካባቢው መሰወራቸውን ጠቁመዋል።

የልጆቻቸው እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል በሚል ለማጣራት ቢሞክሩም ኮሌጁ አድራሻ በማጥፋቱ እንዳልተሳካላቸው በማመልከት ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

የልጆቻቸውን ጊዜና ገንዘባቸውን በከንቱ የነጠቋቸው የኮሌጁ አካላት ላይ መንግስት ተገቢውን ክትትል በማድረግ መፍትሄ እንዲሰጣቸው መፈለጋቸውን ተናግረዋል።

የኮሌጁ አካላት ኢዜአ ስለጉዳዩ ምላሽ እንዲሰጡ ለማነጋገር ጥረት ቢያደረግም አድራሻቸውን ማግኘት አልቻለም።

የተማሪዎችንና ወላጆችን ቅሬታ በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገርናቸው የደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ የተቋማት አቅም ግንባታና የሥልጠና ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ፈቱ  ናስር  በበኩላቸው ጉዳዩን ለማጣራት ክትትልና የማጣራት ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን በተደረገው የማጣራት ስራ  በቢሮው እውቅናም ሆነ ይሁንታ ሳያገኝ ማስተማር  መጀመሩን እንደደረሱበት  ጠቅሰው ይህም አግባብነት ስለሌለው በቀጣይ የተማሪዎቹን እጣ ፋንታ በተመለከተ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ  አስታውቀዋል።

አሁኑ ወቅት  ቡድንና ባለሙያ  ወደ አካባቢው በመጓዝ የተተጀመረው የማጣራት ስራ  በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለቅሬታ አቅራቢዎቹ ተገቢው ምላሽ እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች በከፍተኛ ትምህርት መስክ በተሰማሩ የግል ተቋማት ላይ የማጣራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አመላክተዋል።

በየትኛውም መልኩ ያለ ህጋዊ ፈቃድ እና ማረጋገጫ በተለያየ መልኩ ማስታወቂያዎችን በማስነገር ወደ መማር ሥራ  የሚገቡ   የግል ተቋማት  ህብረተሰቡ በመጠቆም እንዲተባበርም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም