የኮቪድ-19 የህሙማንና የጤና አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችን ደህንነት መጠበቅ ወሳኝ እንደሆነ አሳይቷል

251

አዲስ አበባ ፣መስከረም 8/2013 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሕሙማንና የጤና አገለግሎት ሰጪዎችን ደህንነት መጠበቅ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አጉልቶ ያሳየ ነው ተባለ።

የዓለም የሕሙማን ደህንነት ቀን በዓለም አቀፍና በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ “ደህነንቱ የተጠበቀ የጤና አገልግሎት ሰጪ ሠራተኛ፤ ደህንነቱ የተጠበቀ ታካሚ” በሚል ቃል ትናንት ተከብሯል።

የዓለም የጤና ድርጅት በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም ባደረገው 72ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የዓለም የሕሙማን ደህንነት ቀን በየዓመቱ እንዲከበር በመወሰን ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ተከብሯል።

ትናንት ማምሻውን የሕክምና ባለሙያዎችና ህሙማንን በማስታወስ ጧፍ የማብራት ሥነ ስርዓት በሚሊኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 የህክምና ማዕከል ተካሄዷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውንና ከነዚህም ውስጥ 10 በመቶ የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎች መሆናቸው ተመልክቷል።

በኢትዮጵያም ከ1 ሺህ 400 በላይ የጤና አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውንና የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

 የዓለም የህሙማን ደህንነት ቀን ሲከበር የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የህሙማንና የሕክምና ባለሙያዎች ደህንነት ያላቸውን ትስስር አስመልክተው ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሁለቱም ያላቸው ቁርኝት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ይበልጥ ጎልቶ መውጣቱን ተናግረዋል።

“የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎችን ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው እየሰሩ ነው” ብለዋል።

የጤና ባለሙያዎች ለህሙማን ክብካቤ በሚያደርጉበት ወቅት ደህንነታቸው አደጋ ላይ እንደሚወድቅና ለችግር እንደሚጋለጡም ተናግረዋል።

የህሙማንና የህክምና ባለሙያዎችን ደህንነት መጠበቅ ላይ ገና ብዙ ሥራ ማከናወን እንድሚጠበቅና መንግስትም አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ነው ዶክተር ሊያ የገለጹት።

ደህንነትን የመጠበቅ ጉዳይ የመንግስት ድርሻ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ርብርብ አስፈላጊ እንደሆነም አመልክተዋል።

ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው አገልግሎት እየሰጡ ላሉ የጤና ባለሙያዎች ዶክተር ሊያ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ተግባሩ ይግዛው በበኩላቸው የጤና ባለሙያዎች ደህንነት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስላለ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

የህክምና ባለሙያዎችንና የህሙማን ደህነንት ለመጠበቅ ዘላቂነት ያለው የጤና አጠባበቅ ስርአት ሊኖር እንደሚገባ አመልክተዋል።

“የህክምና ባለሙያዎች ባለባቸው የሥራ ጫና ለስነ ልቦናና ስነ አዕምሯዊ ቀውስ እንዳይጋለጡ አስፈላጊው ክትትል ሊደርግላቸው ይገባል ብለዋል።

የሚሌኒየም የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ኃላፊ ዶክተር እስማኤል ሸምሰዲን በማዕከሉ ዓለም አቀፍ መስፈርትን በጠበቀ መልኩ የሕሙማንና የጤና ባለሙያዎችን ደህንነት ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም የህሙማን ደህንነት ቀን በሚታሰብበት ወቅት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ስለ ህክምና ባለሙያዎች ደህንነት ሊገደው እንደሚገባና አጀንዳ አድርጎ መወያያት እንዳለበት ተናግረዋል።

በሚሌኒየም የኮቪድ-19 የህክምና ማዕከል በተካሄደው የጧፍ ማብራት ስነ ስርዓት ቀኑን አስመልክቶ የተለያዩ መልዕክቶች ተላልፈዋል።