በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በዋግ ኽምራ ዞን ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎት ሰጡ

22

ሰቆጣ፣  መስከረም 8/2013 (ኢዜአ)  በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ባለፉት የክረምት ወራት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው አገልግሎት መስጠታቸውን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ሴቶችና ሕፃናት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የወጣቶች ማካተትና ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ ሙሉጌታ ስኳር ለኢዜአ እንደገለጹት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

“በዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባርም ከ91 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ችግኝ ተከላ፣ የአረጋውያንን ቤት በማደስና መሥራት እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ የግንዛቤና የቅስቀሳ ሥራዎች ተከናውነዋል”ብለዋል።

“በተለይም ደግሞ የኮሮና ቫይረስ መስፋፋትን ተከትሎ በምግብ ራሳቸውን ለማይችሉና ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ በተደረገው እንቅስቃሴ ከስድስት ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ወጣቶቹ አስተባባሪነት ተሰብስቧል”ብለዋል።

በዚህም ከ300 በላይ ለሚሆኑ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ዱቄትና ዘይት ድጋፍ እንደተደረገላቸውም ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት በተከናወኑት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችም ለእነዚህ የልማት ሥራዎች ከመንግሥት ይወጣ የነበረውን ከ3 ሚሊዮን 656 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል። 

በደሃና ወረዳ የአምደወርቅ ከተማ ነዋሪ ወጣት እምወደው ሲሣይ የዕረፍት ጊዜውን ከ500 በላይ ወጣቶችን በማስተባበር የበጎ ፍቃድ ተግባራትን እያከናወነ ማሳለፉን ተናግሯል።

በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ኅብረተሰቡን ግንዛቤ በመስጠትና በገበያ ቦታዎች እጅ በማስታጠብ በጎ ተግባራትን ማከናወናቸውን ተናግሯል።

“የአምደወርቅ እብናት በክረምት ጎርፍ ምክንያት ጉዳት የደረሰበትን የጠጠር መንገድ ለመጠገን ከወጣቶች ባሻገር የወረዳውን ፖሊስ አባላት በማስተባበር የጥገና ሥራ ተከናውኗል”ብሏል።

“በጎ ፍቃድ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ተምሳሌት ነው” ያለው ወጣት እምወደው፤ ቤትና መጠለያ ላልነበራቸው 22 አረጋውያን ከኅብረተሰቡ በሰበሰቡት ገንዘብና ግብዓት ቤት ሠርተው ማስረከባቸውንም ገልጿል።

”በበጎ ፍቃድ ተግባር ላይ በመሳተፌም የኅሊን እርካታንና ማኅበራዊ ወገኝተኝነቴን አሳድጎልኛል” ብሏል፡፡

በአምደ ወርቅ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እማሆይ እቴነሽ ንጋቱ በበኩላቸው ለበርካታ ዓመታት መጠለያ ቤት ስላልነበራቸው ኑሯቸውን በቤተክርስቲያን ተጠልለው ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ክረምት በገባ ቁጥር ይቸገሩ እንደነበር ጠቅሰው፤ ዘንድሮ ወጣቶች መጠለያ ቤት ሠርተው በመስጠታቸው ችግራቸው በመቃለሉ ለበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ምሥጋና አቅርበዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 97 ሺህ 293 ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ በማሳተፍ ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከት እንደተቻለ ከዞኑ ሴቶችና ሕፃናት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።