ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው ተከስቶ በነበረው ሁከት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረገ

ሀረር፣ መስከረም 7/2013(ኢዜአ) ሀረማያ ዩኒቨርስቲ በአካባቢው ተከስቶ በነበረው ሁከት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የግንባታ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ተሳትፎና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር አድማሱ ቦጋለ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ተከትሎ በሀረማያ ከተማ ባቴ 03 ቀበሌ በተፈጠረው ሁከት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል።

ከዚህ በፊት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የምግብ ቁሳቁሶች እንዲሁም ፍራሽ፣ አንሶላና ብርድ ልብስ በወቅቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

“አሁን ከ516 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ 1 ሺህ 124 የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ 66 ከረጢት ሲሚንቶ እና 238 ኪሎግራም ሚስማር በቀበሌው ሊቀመንበር በኩል በተጎጂ ወገኖቹ ለተቋቋመው ኮሜቴ አስረክበናል”ብለዋል።

“ዩኒቨርሲቲው በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የግንባታ ቁሳቁስ እና ሌሎች ድጋፎች ማድረጉን ጠቁመው፤ በቀጣይም ተቋሙ እያደረገ ያለው ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።

በሀረማያ ከተማ የባቴ 03 ቀበሌ ሊቀመንበሩ አቶ ሬድዋን ረሺድ እንደተናገሩት የአካባቢው ነዋሪ በዘርና በሃይማኖት ሳይለያይ ለዘመናት አብሮ የኖረ ማህበረሰብ ነው።

“ሆኖም ፍላጎታቸው ያልተሳካላቸው ስልጣን ፈላጊ አካላት ባቀናበሩት ሴራ ከወራት በፊት በተፈጠረው ሁከት በቀበሌው በ86 ሰዎች ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፤ ከዚህ ውስጥም የ48 ሰዎች ንብረት ሙሉ በሙሉ ወድሟል” ብለዋል።

ችግሩ ከተከሰተ ወዲህም የአካባቢው ማህበረሰብ ተጎጂዎችን በመደገፍ አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ ፤ በተለይ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ከሀረማያ ከተማ ጋር በመተባበር የተጠናከረ ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ተጎጂዎችን በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ከማድረግ አንፃርም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በአካባቢው መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ እየተሰራ መሆኑንና አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራውም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።

ከተጎጂዎች መካከልም አቶ ሃይሌ አበበ የተባሉ የቀበሌው ነዋሪ በበኩላቸው "በንግድ ስራ ተሰማርቼ ስሰራ ነበር ሆኖም ከወራት በፊት በተከሰተው ሁከት ንብረቴ ሙሉ በሙሉ ወድሟል"ብለዋል።

ከመንግስት፣ ከተለያዩ አካላትና ተቋማት ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቁመው፤ በተለይ ዩኒቨርስቲው ችግሩ ከተከሰተ ጀምሮ በርካታ ድጋፍ በማድረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

መንግስት ድጋፉን ከዚህ በተሻለ ማጎልበት ይገባዋል ያሉት አቶ ሃይሌ ዩኒቨርስቲውም ተጎጂዎችን በዘላቂነት ከማቋቋም ጋር ተያይዞ እገዛውን እንዲያጠናክር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

“ተወልጄ ያደግሁት እዚሁ ቀበሌው ነው የተፈጠረው ችግርም የትኛውንም ብሔርና ሃይማኖት እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብ አይወክልም” ያሉት ደግሞ ሌላዋ ተጎጂ ወይዘሮ ስንታየሁ ተመስገን ናቸው።

በተለይም ዩኒቨርሲቲው በችግሩ ለተጎዱ ዜጎች የተለያዩ የምግብ፣ የአልባሳትና የግንባታ ቁሳቁሶች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው ፤ በቀጣይም እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም