በህገ-ወጥ መንገድ ከሃገር ሊወጡ የነበሩ 50 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

74

ጎንደር መስከረም 7/2013(ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በህገ-ወጥ መንገድ ከሃገር ሊወጡ የነበሩ 50 ወጣት ሴቶችና ሶስት ተጠርጣሪ አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንስፔክተር እየሩስ አስማረ ለኢዜአ እንደተናገሩት በቁጥጥር ስር የዋሉት በከተማዋ  ሶስት ሆቴሎች ውስጥ ተደብቀው ነው፡፡

ትናንት ማታ አራት ሰዓት አካባቢ በህብረተሰቡ ጥቆማ የተያዙት እነዚህ ወጣት ሴቶች ከደቡብ ክልል እንደመጡ  ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ማረጋጋጡን አስታውቀዋል፡፡

በህገ-ወጥ መንገድ ያመጧቸው ናቸው የተባሉ ሶስት  ተጠርጣሪ አዘዋዋሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ኢንስፔክተር እየሩስ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሌሎች በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውሩ ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ ግለሰቦችን ለመያዝ ፖሊስ ክትትል እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ተታለው የመጡትን ሴቶች በቀጣዮቹ ቀናት ወደ ትውልድ ስፍራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም