ያሳለፍነው ዓመት የኢትዮጵያ አትሌቶች ለከፋ ችግር የተጋለጡበት ዓመት ነበር

63

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ)  ያለፈው የ2012 ዓመት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለከፋ ችግር የተጋለጡበት ዓመት እንደነበር የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ገለጸ።

የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር በዛሬው እለት ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል።

በጉባኤው ያለፈውን ዓመት የሥራ ክንውንና የፋይናንስ ሪፖርት እንዲሁም የ2013 ዓ.ም የሥራ ዕቅድና ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱም የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አትሌት ማርቆስ ገነቴ ያለፈው 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በኢኮኖሚና በስነ-ልቦና ጫና ለከፋ ችግር የተጋለጡበት ዓመት እንደነበር ገልጿል።

ኮሮናቫይረስ በአገራችን መከሰቱን ተከትሎ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ውድድሮች በመሰረዛቸው፣ አንዳንዶቹም ለሌላ ጊዜ በመሸጋገራቸው ምክንያት አትሌቶቹ ከውድድር ርቀዋል።

"ይህም በተለያዩ ውድድሮች ተሳታፊ በመሆን በአሸናፊነት ካጠናቀቁ  የሚያገኙትን ክብርና የገንዘብ ሽልማት አሳጥቶቸዋል" ብሏል።

እንዲሁም ክለብ የሌላቸው በግላቸው የሚሮጡ አትሌቶች እና ክለብ ያላቸው በርካታ አትሌቶችም በክለቦቻቸው የመሰናበት እጣፋንታ እንደገጠማቸው ተናግሯል።

አትሌቶችን ካሰናበቱ ክለቦች መካከልም ሃዋሳ ከተማ ፣ ሲዳማ ከተማ፣ ጌታ ዘሩ፣ መብራት ኃይል እና ንግድ ባንክ የሚጠቀሱ መሆናቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር በእዚህና ሌሎች ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ አትሌቶችን ለመደገፍ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራቱንም አትሌት ማርቆስ ተናግሯል።

ከሥራዎቹ መካከል አቅም ያላቸው አትሌቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ የማስተባበርና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም የአትሌቶቹን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት 8 ሚሊዮን ብር ያህል ለችግር ለተጋለጡና በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ የፕሮጀክት፣ የብሔራዊ ቡድን እና አንጋፋ አትሌቶች ጭምር ድጋፍ መደረጉን በማሳያነት ገልጿል።

"ይህ ተግባር በጥሩ ጎኑ የሚነሳ ቢሆንም፣ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍና ለሁሉም ተደራሽ በመሆን በኩል ውስንነት ነበር" ብሏል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች ማህበሩ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ያለው መልካም ግንኙነት እና ተቀራራቦ የመሥራት ልምዱን በጥሩ ጎኑ አንስተዋል።

የአትሌቶችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚያከናውነውን ተግባር በቀጣይ ለማጠናከር የበለጠ መሥራት እንዳለበት አመልክተዋል።

ማህበሩ ከፌዴሬሽኑ ብቻ ከሚያገኘው የገንዘብ ድጎማና ድጋፍ በተጨማሪ የራሱን የገንዘብ አቅም ለማሳደግ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባውም ጠቁመዋል።

አትሌቶች ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም በአግባቡ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል በአንዳንድ የአትሌት ማናጀሮች የሚሠራው ሥራም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተወያዮቹ አንስተዋል።

ጉባኤው አትሌቶችን እያበረታቱ ለሚገኙት ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ማህበር፣ የተቸገሩ አትሌቶች ድጋፍ እንዲያገኙ አቅም ካላቸው ሰዎች ጋር በማገናኘት በጎ ተግባር እየሰሩ ላሉት አቶ ሲሳይ ማሞ፣ እንዲሁም በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ አትሌቲክስ ነክ የሆኑ ፈጣን መረጃዎችን ለሚያደርሱት አቶ ወንድማገኝ ጌታቸው የእውቅና የምስክር ወረቀት በመስጠት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም