ኮሚሽኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠሙ ክስተቶች እንዳሳሰቡት ገለጸ

56

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የፀጥታ መደፍረሶችን ተከትሎ ያጋጠሙ ክስተቶች እንዳሳሰቡት ገለጸ፡፡

የፖለቲካ ቡድኖችና ባለድርሻ አካላት ገንቢ ውይይት እንዲያደርጉና ከሁከት ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ኮሚሽኑ ከክልሉ ከመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ አጳር ቀበሌ እንዲሁም ከወንበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ አሳሳቢ መረጃዎች እየደረሱት መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በጳጉሜ 1 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሁም ከጳጉሜ 2 ቀን 2012 ዓም እስከ መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም መካከል ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግስት ለማረጋገጥ መቻሉን ጠቅሷል፡፡

በስፍራው ከሚገኝ መንግስታዊ ምንጭ ቢያንስ በሁለት ዙር በደረሱ ጥቃቶች ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ ግድያዎች መፈፀማቸውን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

የክልሉ መንግስት ከተፈናቃዮቹ መካከል 300 ያህሉ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውንና የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር አካባቢውን ለማረጋጋት እየሰሩ መሆኑን ማሳወቁንም ገልጿል፡፡

ስለሆነም ኮሚሽኑ፡-

● በክልሉ ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ የደረሱትን ጥቃቶች፣ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ሙሉ በሙሉ ያወግዛል፤

● በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር በመከላከያ ሰራዊት፣በፌዴራል ፖሊስ እና በክልል የጸጥታ ኃይሎች ሰላምን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት ያበረታታል፤

● በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግስትና እንዲሁም ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው የቃል ኪዳን ሰነዶች ማለትም፡ በአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ በአለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው የሰብአዊ መብቶት ሰነዶች የተደነገጉትን በሕይወት የመኖር መብቶች እንዲከበሩ ይጠይቃል፤

● በክልሉ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ማጋጠማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ገለልተኛ፣ ፈጣን እና ውጤታማ ምርመራዎችን  በማካሄድ ግድያው በተከሰተባቸው ሁኔታዎች ላይ የጥፋተኞችን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጡ ያሳስባል፤

● የሚመለከታቸው የክልሉ መንግስት አካላት ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ወደ ቀደመ ህይወታቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ጥሪ ያቀርባል፤

● ኮሚሽኑ በተለይም መሰረታዊ የሆነው በህይወት የመኖር መብት ይረጋገጥ ዘንድ የሚመለከታቸው የክልሉ የመንግስት አካላት እንዲሰሩ ያሳስባል፤ የሚሉ ነጥቦችን ለኢዜአ በመግለጫው አካትቶ ልኳል፡፡


በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች እና ባለድርሻ አካላት ገንቢ ውይይት እንዲያደርጉ እና ከማንኛውም ዓይነት የሁከት ድርጊቶች እንዲታቀቡ ሲልም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሁሉም አካላት በሕገ-መንግስቱ የተቀመጡና እና ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውን ሌሎች አግባብነት ያላቸውን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ የተቀመጡ መብቶችን እና ግዴታዎችን እንዲያከብሩ ኮሚሽኑ ጠይቋል፡፡

ኮሚሽኑ በቀጣይም ጉዳዩን በንቃት እንደሚከታተለው አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም