ኤጀንሲው በጥሬ ገንዘብ ንብረት ሽያጭና የብድር ውሎችን አያስናግድም

434

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ) የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በብድር፣ በሽያጭ እና ስጦታ ላይ የሚካሄዱ ውሎችን ሰነድ አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ላይ የአሰራር ለውጥ ማድረጉን አስታውቋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴን ስርዓት ለማስያዝ በመንግስት በኩል የተደረጉ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ኤጀንሲው የአሰራር ማሻሻያ ማድረጉን ተናግረዋል።

የአሰራር ማሻሻያ የተደረገው  ህገወጥ ገንዘብ ወደ ንብረትነት እንዳይለወጥ ለማድረግ በሚል መሆኑንም ገልፀዋል።

የማይንቀሳቀስ ሀብት እንደ መኖሪያ ቤት፣ ድርጅት፣ የሊዝ መብት ሽያጭና የአክሲዮን ድርሻ ማስተላለፍ ሲሆኑ ተንቀሳቃሽ ሀብት ደግሞ እንደ ተሽከርካሪ ያሉትን እንደሚያካትት ተናግረዋል።

በመሆኑም የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል እንዲሁም የብድር ውሎችን ሰነድ አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ኤጀንሲው የሚሄዱ ተገልጋዮች ሊከተሏቸው የሚገቡ አሰራሮችን ዳይሬክተሩ ዘርዝረዋል።

በእዚህም የሽያጭ ዋጋ ወይም የብድር ገንዘብ አከፋፈልን በተመለከተ ክፍያው መፈጸም ያለበት በባንክ ሒሳብ ቁጥር ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በሽያጭ ውል ጊዜ የሽያጭ ዋጋው ባንክ ከሚገኝ የገዢ ሒሳብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ሻጭ የባንክ ሒሳብ የተላለፈ መሆን እንዳለበት ነው የገለጹት።

በብድር ውል ጊዜ ደግሞ የብድሩ ገንዘብ ባንክ ከሚገኝ የአበዳሪ ሒሳብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ተበዳሪ የባንክ ሒሳብ የተላለፈ መሆን እንዳለበት አቶ ሙሉቀን አስረድተዋል።

ህገ ወጥነትን ለመከላከል ሲባል ሌሎች የአሰራር ማሻሻያዎች እስኪደረጉ ድረስ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረትን በስጦታ የማስተላለፍ ውል አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎትንም ኤጀንሲው ላልተወሰነ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ ሙሉቀን እንዳሉት እስካሁን ድርስ ወደ ኤጀንሲው ከሚመጡ ተገልጋዮች አምስት በመቶ ያህል ብቻ የሚሆኑት የስጦታዎች ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ለማግኘት የሚመጡ ናቸው።

ቀሪዎቹ 95 በመቶ የሚሆኑት በሽያጭ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ለማግኘት እንደሚመጡ አመልክተዋል።

“ይሄን የአሰራር ማሻሻያ ተከትሎ ሀሰተኛ ሰነድ እና የሥም ዝውውር ሊያደርጉ የሚችሉ ህገ ወጦችን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት እየተሰራ ነው” ብለዋል።

የአሰራር ማሻሻያው ከዛሬ መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉቀን አመልክተዋል።