በክልሉ በመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው ከ6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት 94 በመቶ በሰብል ተሸፍኗል

86

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ)  በኦሮሚያ ክልል በመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው ከ6 ነጥብ 1ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ 94 በመቶ የሚሆነው በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቀሪው 6 በመቶ መሬት በቀጣይ ጊዜያት በጥራጥሬ ሰብሎች እንደሚሸፈን ተመልክቷል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በክልሉ በ2012/2013 የምርት ዘመን ከ191 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው።

በመኽር እርሻው ለምርት ማሳደጊያ የሚያግዙ የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም፣ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እንዲሁም ግብርናውን የሚያዘምኑ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

አቶ ዳባ እንዳሉት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት በሚፈለገው መጠን ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል።

በምርት ዘመኑ የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት እንደገጠመም ጠቁመዋል፡፡

የፀረ አረም ኬሚካሎች ስርጭትን በተመለከተም 76 በመቶ ለሚሆኑ የክልሉ አርሶ አደሮች መከፋፈሉን ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ ግብርናውን ለማዘመን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በግብርና ስራው በተለይ ስንዴ፣ የቢራ ገብስ፣ ጤፍና በቆሎ በቀዳሚነት እየለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክረምቱ በክልሉ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን አያይዘው የገለጹት አቶ ዳባ ፤ በዚህም አርሶ አደሩ የቡና፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን መትከሉን አመልክተዋል።

ኃላፊው ጨምረው እንደተናገሩት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በምርት ዘመኑ ከ300 ሺህ የሚበልጥ ሄክታር መሬት ላይ በሜካናይዝድ እርሻ በመታገዝ ስንዴ በመስኖ ለማምረት ዝግጅት ተደርጓል።

ለዚህም 2 ሺህ 900 ትራክተሮች፣ 8 ሺህ የውሃ ፓምፖች እንዲሁም ምርጥ ዘር መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።

"በክረምቱ የታየው ከመጠን ያለፈ ዝናብ በተወሰኑ አካባቢዎች ሰብሎችን በመጉዳቱ ጉድለቱን ለመሙላት መሬቱ ቶሎ በሚደርሱ ሰብሎች ይሸፈናል" ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ ከአርሶ አደሩ በተጨማሪ ለ600 ሺህ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርም ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የከተማ ግብርና ለማከናወን ከ290 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙንም አቶ ዳባ ጠቅሰዋል።

በከተማ ግብርና አትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት እርባታ፣ የዶሮ፣ የአሣ እና ንብ የማነብ ሥራዎች እንደሚከናወኑም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም