በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ ልዑክ አዲስ አበባ ገባ

100
ሐምሌ 7/2010 በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ ልዑክ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ  ደማቅ አቀባበል ተደረገለት። በፕሬዚዳንቱ የሚመራውን ልዑክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣የባህል ቡድን፣ የፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንድ፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት፣ የኃይማኖት አባቶች እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ፕሬዚዳንቱ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባቀረቡላቸው ግብዣ መሰረት ነው። በቆይታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር አብሮ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋሉ። ልዑኩ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ  ጉብኝት እንደሚያደርግም ይጠበቃል። የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ትናንት እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ያለው የኤርትራ ኤምባሲ የማደስ ሥራው ተጠናቆ ይፋዊ የመክፈኛ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ወይም ከነገ በስቲያ ይካሄዳል። ኤምባሲው የሚከፈተው  የኤርትራ ልዑክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር የደረሱትን ሥምምነት ተከትሎ መሆኑንም ነው የገለጹት። በቅርቡም ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን በአስመራ እንደምትከፍት ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የአሰብ ወደብን ለመጠቀም የዝግጅት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከቀናት በኋላ ወደ አስመራ የቀጥታ በራራ ይጀምራል ብለዋል። ሌሎችም ተመሳሳይ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በማከናወን የአገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነት የተሳለጠ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። ከዛ ባለፈ አገራቱ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በመቋቋም በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የትብብር መስክ ዳግም ለመመለስ እየተሰራ ነው ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሃምሌ 1/2010 ዓ.ም ወደ ኤርትራ አምርተው የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር መፈራረማቸው ይታወሳል። ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ጦርነት በይፋ እንዲቆም፣ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ በባህልና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን ለማደስ የሚያስችል መሆኑም በወቅቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም