በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ የሰሊጥ ምርታማነትን ማሳደግ እንደቻሉ አርሶ አደሮች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ የሰሊጥ ምርታማነትን ማሳደግ እንደቻሉ አርሶ አደሮች ተናገሩ
መተማ፣ መስክረም 6/2013 (ኢዜአ) የግብርና ባለሙያዎች የሚያደርጉላቸውን ሙያዊ እገዛ በመጠቀም የሰሊጥ ምርታማነት ማሳደግ እንደቻሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን ሰሊጥ አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ።
በዞኑ መተማ ወረዳ ለምለም ተራራ በኩታ ገጠም የለማን የሰሊጥ ማሣ የመስክ ጉብኝት ተካሄዷል።
በወረዳው የለምለም ተራራ ቀበሌ አርሶ አደር ቃሲም ኢብራሂም በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ቀደም ሲል የሰሊጥ ልማት የሚያከናውኑት በልማዳዊ አሰራር ነበር።
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በግብር ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ምክረ ሀሳብ ተቀብሎ በመተግበር የሰሊጥ ምርታማነትን ማሻሻል እንደቻሉ ተናግረዋል።
በዚህም የማሣቸውን ጥቁር አፈር አንጣፈው፣ በቂ ግብዓት በመጠቀምና በመሥመር በመዝራት በሁለት ሄክታር መሬት 20 ኩንታል የሰሊጥ ምርት ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል።
ከዚሁ መሬት ቀደም ሲል ያገኙት የነበረው ምርት ከሦስት ኩንታል እንደማይበልጥ አስታውሰው፤ የግብርና ባለሙያዎች የሚያደርጉላቸውን ሙያዊ እገዛ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚ እንደሆኑ አስረድተዋል።
''መሬቱን በአግባቡ በማጽዳት ጥቁር አፈሩን አንጣፍፌና ግብዓት ተጠቅሜ በመዝራቴ ዝናቡ ቢበዛም ምንም ዓይነት ጉዳት አላደረሰብኝም'' ያሉት ደግሞ ሌላኛው የቀበሌው አርሶ አደር ያሲን ሰዒድ ናቸው።
ከዚህ በፊት ሰሊጥ ለምቶበት የማያውቀውን መሬት ላይ ያለውን ጥቁር አፈር በማንጣፈፍ የተሻለ ምርት የሚሰጥ ሰሊጥ ማልማታቸውን ተናግረዋል።
አራት ሄክታር መሬታቸውን በኩታ ገጠምና በመሥመር በመዝራታቸው ቀደም ብሎ ከሦስት ኩንታል በላይ ምርት በሄክታር የማያገኙትን ባለፈው የመኸር ወቅት ካለሙት ዘጠኝ ኩንታል የሰሊጥ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የጋብላ ቀበሌ አርሶ አደር አየነው ጎባለ በበኩላቸው 40 ሆነው በመደራጀት በኩታ ገጠም 78 ሄክታር መሬት እያለሙ መናቸውን አስረድተዋል።
ከሚለማው መሬት ውስጥ ሁለት ሄክታር መሬት የእሳቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህም 18 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
''በቂ ግብዓትን በመጠቀም በኩታ ገጠም ማልማት ያለውን ልዩነት አሁን በሚገባ ተረድቻለሁ" ብለዋል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌትነት በልሑ እንዳሉት በ2012/2013 የምርት ዘመን 20 ሺህ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 44 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ሰሊጥ እየለማ ነው።
ባለፈው ዓመት 36 ሺህ ሄክታር ብቻ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ለምቶ እንደነበር አስታውሰው፤ በተያዘው የምርት ዘመን በስምንት ሺህ ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።
"ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው እያለሙ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ማሣ በመስክ ጉብኝት መካሄዱም የተሻሻሉ አሰራሮችን ለማስፋፋት ያለመ ነው" ብለዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸሩ ወቅት በሰሊጥ ዘር ከተሸፈነው 165 ሺህ ሄክታር መሬት ከአንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ገልጸዋል።
በመስክ ጉብኝቱ ከሁሉም ወረዳዎች የተወጣጡ አርሶ አደሮች፣ የአዊ ዞንና ማዕከላዊ ጎንደር አዋሳኝ ወረዳዎች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ የዞንና የክልል አመራሮች ተገኝተዋል።