ቀጣዩን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በስድስት ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው

76

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) ቀጣዩን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በስድስት ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የአገልግሎት መተግበሪያ ፖርታል ተግባራዊ እንደሚያደረግ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ባለፉት ዓመታትም በእንግሊዝኛና አማርኛ ቋንቋዎች የተደራጀ የቴክኖሎጂ የመረጃ ቋት መቀመጡ ተገልጿል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አነሳሽነት ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ማከናወን ከጀመረች ሁለት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡

በያዝነው ዓመትም ጅማሬውን ሐዋሳ በማድረግ በባህርዳር በተጠናቀቀው መርሃ-ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ ከአምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኃላፊነቱን ወስዶ እየሰራ እንደሚገኝም ይታወቃል፡፡

ሚኒስቴሩ በሁለት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑትን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በእንግሊዝኛና አማርኛ ቋንቋዎች www.greenlegacy.et በተሰኘ መተግበሪያ ድረ-ገጽ በቴክኖሎጂ እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ቴክኖሎጂውን በቋንቋ ተደራሽ ለማድረግም እንግሊዝኛን ጨምሮ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የፕሮጀክቶች ዳይሬክተር አቶ አቤል ሰለሞን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩን በቴክኖሎጂ ለማገዝ ዝግጅት ተደርጓል።

በመጀመሪያው የትግበራ ምዕራፍ በእንግሊዝኛና አማርኛ ቋንቋዎች በማዘጋጀት የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ መረጃዎች ተደራሽ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂውም ቀደም ሲል በሪፖርት ሂደት የነበረውን የመረጃ ተዓማኒነት ችግር ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ መተግበሪያው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑትን የዝግጅትና ትግበራ ምዕራፍ፣ የክትትል ሂደትና የጽድቀት መጠን በቀላሉ ለመለካትና ለማወቅ እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

የአገልግሎት መተግበሪያ ድረ-ገጽ ከተለያዩ ተቋማት ተውጣጥቶ ከተደራጀው አገራዊ ኮሚቴ ጋር በመሆን የተሰራ መሆኑን አቶ አቤል ጠቁመዋል።

ቴክኖሎጂው በስድስት ቋንቋዎች ተግባራዊ መደረጉ ሁሉም አካል በሚረዳው ቋንቋ በአረንጓዴ አሻራ ዙሪያ የሚተላለፉ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘትና ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ተብሏል፡፡

እንደ አገርም የተደራጀ የመረጃ ቋት መኖሩ በዘርፉ ለሚደረጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም