በክበበ ፀሀይ ህፃናት ማሳደግያ አገልግሎት የሚሰጥ የጨቅላ ህጻናት ማቆያና ክብካቤ ማዕከል ክሊኒክ ተመረቀ

256

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6/2013(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በክበበ ፀሀይ ህፃናት ማሳደግያ አገልግሎት የሚሰጥ የጨቅላ ህጻናት ማቆያና ክብካቤ ማዕከል ክሊኒክ አስመረቀ፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ደጋፊ ያጡ ህፃናትን መንከባከብ የሁሉም ህብረተሰብ ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ተጠቁሟል።

በማዕከሉ ምረቃ ላይ የተገኙት የከተማዋ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በተለያዩ ምክንያቶች ደጋፊና ተንከባካቢ ያጡ ህፃናትን መንከባከብና ማቋቋም የአንድ ተቋም ሀላፊነት ብቻ ሳይሆን የሁሉም አካል መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በከተማዋ በርካታ ህፃናት ተንከባካቢና ደጋፊ አጥተው ኑሯቸውን በተመሰቃቀለ ሁኔታ እንደሚገፉ ያወሱት ወይዘሮ አበበች፤ እነዚህን ህፃናት በመንግስትና በግል ህጻናት ማሳደጊያዎች ውስጥ ብቻ በመንከባከብ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

ህጻናቱ ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው እንዲያድጉ መንግስት አቅሙ የፈቀደውን ያህል እየጣረ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ጥረቱ የሚሳካው በተባበረ የህብረተሰብ ተሳትፎ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀዳስ ኪዱ በበኩላቸው የተከፈተው የጨቅላ ህፃናት ማቆያና ክብካቤ ክሊኒክ በማዕከሉ የሚገኙ ከ140 በላይ ህጻናት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ማዕከሉን ዘመናዊ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ ዘንድሮ በግቢው ውስጥ መድሀኒት ቤት ለመክፈት እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በከተማዋ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ አራት ማዕከላት ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ለጨቅላ ህጻናት ማቆያና ክብካቤ ማእከሉ ማሽኖች ግዢና ለእድሳት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተነግሯል።

ህፃናት በማቆያ ማእከል በብቻ ተወስነው እንዳይቆዩ የተለያዩ የጉዲፈቻ አማራጮችን በመዘርጋት ህጻናቱ ቤተሰባዊ ፍቅር እያገኙ እንዲያድጉ ለማድረግ ቢሮው በመስራት ላይ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ ከ500 በላይ ህፃናት በጉዲፈቻ ተሰጥተዋል።

የክበበ ፀሀይ ህፃናት ማሳደጊያ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በ1956 ዓ.ም ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡና ተጥለው የተገኙ ህፃናትን በመንከባከብ ያሳድጋል።

ተቋሙ ከእውቁ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ባለቤት በወይዘሮ ክበበ ፀሀይ ስም የተሰጠ ግቢ ውስጥ መቋቋሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም